Fana: At a Speed of Life!

በህዳሴ ግድብ ላይ በአፍሪካ ህብረት ውይይት ላይ የተሳተፉት መሪዎች የፀጥታው ምክር ቤት ህብረቱ ጉዳዩ  ይዞ እየተመለከተው መሆኑን እንዲገነዘብ ጠየቁ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የህዳሴ ግደብን በተመለከተ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ የያዙትን ልዩነት በንግግር እንደፈቱ የሚያስችል ድርድር እንዲያደርጉ ያወያየው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ቢሮ በውይይቱ በተደረሱ ውሳኔዎች ላይ ይፋዊ መግለጫ አውጥቷል።

ቢሮው በመግለጫው ሶስቱም ሀገራት ለትናንቱ የአፍሪካ አንድነት ደርጅት ለዛሬው የአፍሪካ ህብረት መመስረት ያበረከቱትን አስተዋፅኦ አውስቷል።

አያይዞም የታላቁ የአትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት የአፍሪካ ሃብት መሆኑን መግንዘባቸውንም ነው ያመለከተው።

በትናንቱ ውይይት ሀገራቱ ግድቡን በተመለከተ ካሉ ጉዳዮች መካከል 90 በመቶ በሚሆኑት ላይ ከስምምነት መድርሳቸውን በተመለከተ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መኸመት ያቀረቡትን ሪፖርት አድንቋል።

በቀሩት ጉዳዮች ላይ ሶስቱም ሀገራት ሰላማዊ መፍትሄ ለመስጠት ያለቸውን ቁርጠኝነትንም አድንቋል።

በቀሩ የቴክኒክና የህግ ጉዳዮች ላይ ሀገረቱ የማያዳግም መፍትሄ እንዲሰጡ ለድርድሩ አዲስ ጉልበት እንደሚሆን መወሰኑን አስታውቋል።

ሶስቱም ሀገራት ድርድሩን ፍሬ ከሚያሳጡ መግለጫዎችና  ድርጊቶች እንዲቆጠቡ አሳስቧል።

ደቡብ አፍሪካ በሊቀመንበርነት የምትመራውና ሶስቱ ሀገራት እና ታዛቢዎች የሚገኙበት በግድቡ ላይ የሚሰራ የሶስትዮሽ ኮሚቴ መቋቋሙና ይህም ኮሚቴ ሪፖርቱን ለወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር እና ለደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ሪፖርት የሚቀርብ ይሆናል።

ቢሮው እና በውይይቱ የተሳተፉት የሀገራት መሪዎች የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የግድቡን ጉዳይ የአፍሪካ ህብረት ይዞ እየተመለከተው መሆኑን እንዲገነዘብ ጠይቀዋል።

ይኸው የመሪዎች ስብስብ በሁለት ሳምንታት ውስጥ የድርድሩን ውጤት ለመመልከት ዳግም እንደሚሰበሰቡ ቢሮው በመግለጫው ጠቁሟል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.