በክልሉ እየተገነቡ ያሉ ግድቦች አርብቶ አደሩን ተጠቃሚ እያደረጉ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ቆላማ አካባቢዎች እየተገነቡ ያሉ አነስተኛና መካከለኛ ግድቦች አርብቶ አደሩ በመስኖ ልማት እንዲሠማራ ዕድል ፈጥረዋል ተባለ፡፡
በክልሉ መስኖና አርብቶ አደር ቢሮ የኮንትራት ፕሮጀክቶችና መስኖ አስተዳደር አስተባባሪ ተመስገን ሩንዳ እንዳሉት÷ በቆላማ አካባቢዎች የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ የሚያስከትለውን ጉዳት በዘላቂነት ለመቋቋም ጥረት እየተደረገ ነው፡፡
ለአብነትም ‘ፊነ ኦሮሚያ’ የሚል ስያሜ ያለው ፕሮጀክት ተነድፎ የመስኖና መጠጥ ውኃ ተደራሽነት ላይ እየተሠራ መሆኑን ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡
በ’ፊነ ኦሮሚያ’ ፕሮጀክትና በመደበኛ የመስኖ ፕሮጀክት ግንባታ በአራት ዓመት 22 ፕሮጀክቶችን በቆላማና ከፊል ቆላማ የአርብቶ አደር አካባቢዎች መገንባት መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
አገልግሎት መስጠት ከጀመሩት ፕሮጀክቶች መካከል 18 ያህሉ ቆላማ አካባቢ በሆኑት ቦረናና ምስራቅ ቦረና፣ ጉጂ፣ ምስራቅ ባሌ፣ ምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ ዞኖች መገንባታቸውን ገልጸዋል፡፡
አነስተኛ የመስኖ ግድቦቹ የዝናብ ውኃን በመያዝ ከሰውና እንስሳት መጠጥ ውኃ አቅርቦት ባለፈ አርብቶ አደሩ በስፋት በመስኖ ልማት እንዲሠማራ እያስቻሉ ነው ብለዋል፡
የተገነቡ ግድቦች እስከ 80 ሚሊየን ሜትር ኪዩብ ውኃ የመያዝ አቅም እንዳላቸው ጠቅሰው÷ አካባቢው ወደ ልማት እንዲገባ፣ አረንጓዴና ሥነ-ምኅዳሩ የተጠበቀ እንዲሆን በማድረግ ረገድም ወሳኝ ሚና አላቸው ነው ያሉት፡፡