ኢሬቻ በድምቀት እንዲከበር የፀጥታና ደኅንነት አካላት ወደ ሥራ መግባታቸው ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ እና በቢሾፍቱ ከተሞች የሚከበሩ የኢሬቻ በዓላት ያለምንም የጸጥታ ሥጋት በድምቀት እንዲከበሩ የፀጥታና ደኅንነት አካላት ቅድመ ዝግጅታቸውን አጠናቅቀው ወደ ሥራ መግባታቸው ተገለጸ፡፡
የፀጥታና ደኅንነት አካላት የመስቀል ደመራ በዓልን አከባበር ገምግመዋል፡፡
ከግምገማው በኋላ በሰጡት መግለጫም÷ በተደረገ የተቀናጀ ኦፕሬሽን የመስቀል ደመራ በዓልን ለማደናቀፍ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የሽብርና የፅንፈኛ ቡድኖች አባላትን እኩይ ዓላማ ማክሸፍ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
በዚህም ከጦር መሳሪያዎች፣ ቦንቦች እና የፀጥታ አካላት የደንብ ልብሶች ጋር በቁጥጥር ሥር የዋሉ አካላት ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝ መገለጹን የፌደራል ፖሊስ መረጃ አመላክቷል፡፡
የፊታችን መስከረም 25 እና 26 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባና በቢሾፍቱ የሚከበሩት የሆራ ፊንፊኔ እና የሆራ አርሰዲ ኢሬቻ በዓላትም እሴታቸውን ጠብቀው እንዲከበሩ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ የፀጥታ ኃይል መሠማራቱ ተገልጿል፡፡
የኢሬቻ በዓል ከሚፈቅደው ባህላዊ ስርዓት ተቃራኒ የሆኑ ግጭት ቀስቃሽ ጽሁፎችና መልዕክቶችን ይዞ መገኘት እንደማይቻልም ፖሊስ አሳስቧል፡፡
ሕብረተሰቡ ከፖሊስ የሚተላለፉ የክልከላ መልዕክቶችን በማክበር ፀጥታን የሚያደፈርሱ አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲመለከት የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያን (EFPApp) ወይም በነፃ የስልክ መስመር 991 በመጠቀም ጥቆማዎችን በፍጥነት በመስጠት ወይም መረጃውን በአካባቢው ለሚገኙ የፀጥታ ኃይሎች በአካል በማድረስ የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ ቀርቧል፡፡