ማኅበሩ ከዳያስፖራዎች ያሰባሰበውን አጀንዳ ለኮሚሽኑ አስረከበ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ዳያስፖራዎች ማኅበር በውጭ ከሚኖሩ እና ይኖሩ ከነበሩ ዳያስፖራዎች ያሰባሰበውን አጀንዳ ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስረከበ፡፡
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) አጀንዳዎቹን በተረከቡበት ወቅት÷ በምክክሩ ከአምስቱ ባለድርሻ አካላት መካከል የዳያስፖራው ማሕበረሰብ አንዱ መሆኑን አስታውሰዋል።
ኮሚሽኑ ከዳያስፖራውም ሆነ ከሌሎች አካላት የሚቀርብለትን አጀንዳ ለመቀበል ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠው÷ ለምክክር ሂደቱ መሳካትም ዳያስፖራው የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
የአዲስ አበባ ዳያስፖራዎች ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት ካፒቴን ሰለሞን ግዛው በበኩላቸው÷ ዳያስፖራው ለምክክሩ መሳካት የድርሻውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
ከአጀንዳ ርክክቡ ጎን ለጎንም እንመካከር የተሰኘ የሙዚቃ ክሊፕ በአዲስ አበባ ዳያስፖራዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አርቲስት ዘለቀ ገሰሰ አማካኝነት ለምክክር ኮሚሽኑ ተበርክቷል።
አርቲስት ዘለቀ የኪነ ጥበብ ሥራዎች ተፅዕኖ መፍጠር የሚችሉ በመሆኑ ተመሳሳይ ሥራዎች አስፈላጊ መሆናቸውን በርክክቡ ወቅት ገልጿል።
የሙዚቃ ሥራው በቀጣይ በተለያዩ የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች እንደሚሠራም አመላክቷል፡፡