የምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ መርሐ-ግብር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እያገዘ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) እየተተገበረ ያለው የምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ መርሐ-ግብር በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት እያገዘ ነው ተባለ፡፡
መርሐ-ግብሩ በኢትዮጵያ መንግሥትና በዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ በአብዛኛው የሀገሪቷ ክፍሎች እየተተገበረ እንደሚገኝ ግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
በመርሐ-ግብሩ አፈፃፀም እና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ የሚመክር ሀገር አቀፍ ጉባዔ በድሬዳዋ እየተካሄደ ነው።
የግብርና ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ከተማ በቀለ በጉባዔው ላይ እንዳሉት÷ መርሐ-ግብሩ በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናንና ብልፅግናን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ተግባራትን እያገዘ ነው።
ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲን ከግብ ለማድረስ ከተዘጋጀው የ10 ዓመት የግብርና ልማት ዕቅድ ጋር ተጣጥሞ የሚካሄድ በመሆኑ ምርታማነትን ለመጨመር እያገዘ ነው ብለዋል፡፡
የምግብ ሥርዓትን ስርነቀል በሆነ መንገድ ለመለወጥ፣ የስራ ዕድል ፈጠራን ለማሳደግ እንዲሁም በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ያግዛል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ኢትዮጵያ በመተግበር ላይ የምትገኘውን ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ማህበረሰብ እና ኢኮኖሚ የመገንባት ሂደት በማገዝ ረገድም የጎላ አበርክቶ እንዳለው አስረድተዋል፡፡
እስከ አሁን በመርሐ-ግብሩ የተሻለ አፈፃፀም ቢመዘገብም፤ በቀጣይ በአንዳንድ ዘርፎች የሚታዩ ውስንነቶችን በመለየት፣ የመፈፀም አቅም በማሳደግ፣ የግሉን ዘርፍ በማሳተፍና የገበያ ትስስር በመፍጠር፣ የሚፈለገውን ውጤት ለማስመዝገብ መረባረብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።