Fana: At a Speed of Life!

ኢንጂነር ታከለ ዩኒፎርምን ጨምሮ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ እንዲደረግና የምገባ መርሃ ግብር እንዲተገበር ላበረከቱት አስተዋፅኦ ተሸለሙ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 4 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በከተማዋ በሚገኙ ሁሉም የመንግስት ትምህርት ቤቶች ዩኒፎርምን ጨምሮ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ እንዲደረግ እና የምገባ መርሃ ግብር በዘላቂነት እንዲተገበር ላበረከቱት አስተዋፅኦ ከከተማዋ ወጣቶች ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

ሽልማቱ የተበረከተላቸው “እናመስግን!” በሚል በከተማው ወጣቶች በተዘጋጀው የምስጋና እና የእውቅና መርሃ ግብር ላይ ነው፡፡

የ300 ሺህ ተማሪዎች ምገባን ጨምሮ፣ ለ600 ሺህ የመንግስት ትምህርት ቤት ተማሪዎች የዩኒፎርም እና የትምህርት ቁሳቁስ አቅርቦት እንዲሁም በአስሩም ክፍለ ከተሞች የሚገኙ የአቅመ ደካሞችና አረጋውያን ቤት እድሳት ላይ ላበረከቱት የላቀ አስተዋፆኦ ሽልማት እንደተበረከተላቸውም ተገልጿል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ የተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም ህግ እና ተቋማዊ ይዘት እንዲኖረው እና በዘላቂነት እንዲተገበር ለማስቻል ለካቢኔ የቀረበው ሃሳብ ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት በማግኘቱ ‘የተማሪዎች የምገባ ኤጀንሲ’ እንደሚቋቋም ኢንጂነር ታከለ ተናግረዋል፡፡

የኤጀንሲው መቋቋም በተያዘው የበጀት ዓመት የከተማ አስተዳደሩ በስፋት የሰራውን የተማሪዎች የምገባ ፕሮግራምን ጨምሮ የትምህርት ቁሳቁስ አቅርቦት ቀጣይነት እንዲኖረው እና ተቋማዊ እንዲሆን እንደሚረዳም ነው የተናገሩት።

በመድረኩ ላይ የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬን ጨምሮ የፌደራልና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች እንዲሁም የከተማው ወጣቶች ተሳታፊ መሆናቸውን ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.