ጥንቃቄ የሚሻው የመድሃኒት አወሳሰድ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በምርመራ ለተረጋገጠ በሽታ ትክክለኛው መድኃኒት ለታማሚው በጊዜና መጠን ሲሰጥና ታማሚውም መድኃኒቱን በትክክል ሲወስድ አግባባዊ የመድኃኒት አጠቃቀም ይባላል፡፡
በአንጻሩ በትክክል ተመርምሮ የትኛው ዓይነት በሽታ አምጪ ተህዋስ እንዳስከተለው ለማይታወቅ በሽታ ከታዘዘው መጠን በታች ወይም በላይ ሲወሰድ፣ መወሰድ ከነበረበት ሠዓት ቀድሞ ወይም ዘግይቶ ሲወሰድ፣ የታዘዘውን ጸረ-ተህዋስ መድኃኒት ሙሉ በሙሉ ሳይወስዱ ከቀረ (ከተቋረጠ) ወዘተ አግባባዊ የመድኃኒት አጠቃቀም የለም ይባላል፡፡
መድኃኒትን በአግባቡ አለመጠቀም ደግሞ የተለያዩ ጉዳቶች ያሉት ሲሆን÷ ከእነዚህ ችግሮች አንዱ የጸረ-ተህዋሲያን መድኃኒቶች መላመድ ነው፡፡
ይህም ማለት ከዚህ ቀደም በበሽታ አምጪ ተህዋሲያን አማካኝነት የሚመጡ በሽታዎችን ለማከም ሆነ ለመከላከል ሲሰጥ የነበረው የጸረ-ተህዋስ መድኃኒት ሲሰጥ በነበረው መጠን ወይም ከዚያም በላይ የሰውነትዎ ሴሎች ሊቋቋሙት በሚችሉት መጠን ሁሉ ሲሰጥ ተህዋሲያኑ የማይሞቱ ወይም መራባትን የማያቆሙ እና ታማሚው ከህመሙ የማይፈወስ ከሆነ ተህዋሱ ከመድኃኒት ጋር ተላምዷል ይባላል፡፡
ስለሆነም መድኃኒቱን በተላመደ ተህዋስ የታመመ ህመምተኛ ምንም እንኳ በሽታው በትክክል ታውቆ መድኃኒቱን እየወሰደ ቢሆንም ከበሽታው የማይፈወስ ይሆናል፡፡
የመድኃኒቶች ከጀርሞች ጋር መላመድ ሲባል ደግሞ መድሃኒት የሰውነት ሴሎች በሚቋቋሙት መጠን ሁሉ ሲሰጥ ከሕመም የማይፈወስ ሲሆኑ ነው፡፡
የጸረ-ተህዋሲያን መድኃኒቶች መላመድ የሚባለው ጀርሞች ከጸረ-ተህዋሲያን (ጸረ- ጀርም መድኃኒቶች) ጋር በመላመዳቸው ምክንያት የሚከሰት ችግር ብቻ መሆኑን የአለም ጤና ድርጅት መረጃ አመላክቷል፡፡
ሁሉም የጸረ-ተህዋሲያን መድኃኒቶች ማለትም ጸረ-ባክቴሪያ (አንቲባዮቲክ) መድኃኒቶች፣ ጸረ-ቫይረስ መድኃኒቶች፣ ጸረ ፈንገስ መድኃኒቶች እና ጸረ-ፐሮቶዝዋ በበሽታ አምጪ ጀርሞች እንደሚላመዱም መረጃው አስታውሷል፡፡
ስለሆነም የትኛውንም መድሃኒት ስንወስድ አስፈላጊ የሆኑ የአወሳሰድ መመሪያዎችን ተከትለን ሊሆን እንደሚገባ የህክምና ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡