ቢዝነስ

ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ማዕድናትን በሀገር አቅም ለመሸፈን እየተሰራ ነው

By Tibebu Kebede

July 13, 2020

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ የማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስቴር ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ማዕድናትን በሀገር አቅም ለመሸፈን እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር በመሆን በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድም ተፈራርሟል።

ሁለቱ ተቋማት በጋራ በሚሰሩባቸው ዘርፎች ላይ የመከሩ ሲሆን፤ የማዕድንና ኢንዱስትሪ ስትራቴጂካዊ ትስስር ዕቅድ ላይ ጥናታዊ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

በጥናቱ እንደተመለከተው ከሆነ ኢትዮጵያ ለብረትና ብረት ነክ ግብዓቶች 850 ሚሊየን ዶላር ለኬሚካልና ግንባታ ግብዓት ደግሞ 950 ሚሊየን ዶላር በዓመት ወጪ ታደርጋለች።

ከውጭ የሚመጡ መሰል ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ በመተካትና ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪ ለማስገኘት መስራት እንደሚገባ በዚህ ወቅት ተጠቁሟል።

የማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስቴር በቀጣይ ዓመት የማርብል ግራናይትና ብርጭቆ ምርቶችን መቶ በመቶ በሀገር ውስጥ ለመተካት አቅዶ እየሰራ ይገኛል።

በትእግስት አብርሃም