በክረምት የበጎ ፈቃድ ሥራ 19 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ማዳን ተቻለ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2016 ዓ.ም ሀገር አቀፍ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎትየልማት ተግባራትን በማከናወን 19 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር የሚገመት ሀብት ማዳን መቻሉ ተገለጸ፡፡
“በጎነትና አብሮነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ሐሳብ የተከናወኑ የ2016 ዓ.ም ሀገር አቀፍ የክረምት የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማጠቃለያ መርሐ-ግብር በጅማ ከተማ ተካሂዷል፡፡
በዚሁ ወቅት የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ ሙና አሕመድ እንዳሉት÷ በተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች 52 ነጥብ 7 ሚሊየን የሕብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡
በዚህም በመንግሥትና በማሕበረሰቡ ያልተሸፈኑ የልማት ሥራዎችንና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን በማከናወን 19 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር የሚገመት ሀብት ማዳን ተችሏል ብለዋል፡፡
በ2016 የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎትም 22 ነጥብ 4 ሚሊየን ወጣቶች መሳተፋቸውንም አንስተዋል፡፡
የበጎ ፈቃድ ሥራው ወጣቹ የየክልሉን ባህል፣ ወግ እና እሴቶችን እንዲያውቁ ከማድረጉ ባሻገር÷ እርስ በርስ እንዲተዋወቁና ማኅበራዊ ትስስራቸው እንዲዳብር እድል ፈጥሯል ነው ያሉት፡፡
የኦሮሚያ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ማቲዎስ ሰቦቃ በበኩላቸው በክልሉ 9 ነጥብ 8 ሚሊየን ወጣቶች ያከናውኑት የክረምት በጎ ፈቃድ ሥራ÷ 26 ነጥብ 8 ሚሊየን የሕብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ አድርጓል ብለዋል፡፡
በተስፋሁን ከበደ እና አብዱራህማን መሀመድ