ኢትዮጵያ የአፍሪካውያን ቤት ናት – ፊፋ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2017፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ለአፍሪካ አንድነት ትልቅ ሚና የተወጣችው ኢትዮጵያ የአፍሪካውያን ቤት ናት ሲሉ የዓለም እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ገለጹ።
46ኛው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
የዓለም እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ በጉባዔው ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ኢትዮጵያ በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን (ካፍ) ምስረታ እና ለአፍሪካ አንድነት ትልቅ ሚና መጫወቷን ገልጸዋል።
“ሁሌም ወደ ኢትዮጵያ ስመጣ የአፍሪካ ቤት እንዳለሁ ይሰማኛል” ያሉት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ፥ ወደ ኢትዮጵያ በድጋሚ በመምጣታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡
ፊፋ ለአፍሪካ እግር ኳስ ልማት እና እድገት የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ፕሬዚዳንት ፓትሪስ ሞትሴፔ በበኩላቸው÷ ለአፍሪካ እግር ኳስ እድገት እና ልማት አበክሮ እየሠራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡
የአፍሪካ ሀገራት በዓለም እግር ኳስ ላይ ውጤታማ እየሆኑ እንደሚገኙ ገልጸው፥ በፈረንጆቹ 2022 በኳታር አስተናጋጅነት የተካሄደው 22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ሞሮኮ ለግማሽ ፍጻሜ መድረሷ አንዱ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጅራ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ እግር ኳስ ትልቅ መሰረት የጣለች ሀገር መሆኗን ገልጸው÷ ከካፍ መስራች ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗን አስታውሰዋል፡፡
የአፍሪካ ዋንጫን ሦስት ጊዜ በማስተናገድ አንድ ጊዜ ዋንጫ ማንሳቷን አውስተው፥ ይድነቃቸው ተሰማ የካፍ ፕሬዚዳንት በነበሩበት ወቅት ለአፍሪካ እግር ኳስ እድገት ትልቅ ሚና መጫወታቸውን ተናግረዋል።
46ኛው የካፍ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ በአሁኑ ሰዓት የፋይናንስ የአፈጻጸምን ጨምሮ የተለያዩ ሪፖርቶችን በማዳመጥ ይገኛል።
ጉባዔው በአፍሪካ እግር ኳስ ጉዳዮች ላይ በመወያየት የተለያዩ ውሳኔዎች ያሳልፋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ኢዜአ ዘግቧል፡፡