በሳምንቱ መጨረሻ በተካሄዱ ውድድሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ቀንቷቸዋል
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 6፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ባለፍነው ቅዳሜና እሁድ በተለያዩ ሀገራት በተካሄዱ የአትሌቲክስ ውድድሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ቀንቷቸዋል።
በቻይና በተካሄደ የሼንዚን የወንዶች ማራቶን ውድድር ታደሰ ቶላ እና ተረፈ ደበላ ተክታትለው በመግባት ከአንድ እስከ ሁለተኛ ያለውን ደረጃ ሲይዙ በቀለ ሙሉነህ ሰባተኛ በመሆን ውድድሩን አጠናቋል።
በተመሳሳይ በሴቶች የማራቶን ውድድር በላይነሽ ያሚ፣ መድህን ግብረስላሴ እና ፀሃይ ደሳለኝ ተከታትለው በመግባት ከአንድ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ ሲይዙ ኑሪት ሽመልስ አራተኛ፣ በሻዱ በቀለ ስድስተኛ በመግባት ውድድሩን አጠናቀዋል።
እንዲሁም በስፔን በማላጋ በተካሄደ የማራቶን ውድድር በሴቶች አትሌት ሰላማዊት ጌትነት እና አትሌት ገላን ሰንበቴ 1ኛ እና 2ኛ ደረጃን በመያዝ ተከታትለው በመግባት አሸናፊ ሆነዋል።
በተመሳሳይ በታይላንድ በቴፒይ ማራቶን በሴቶች መስከረም አበራ ውድድሩን 1ኛ በመግባት በበላይነት ስታጠናቅቅ ቆንጂት ጥላሁን በአራተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን አጠናቃለች።
በተጨማሪ በቡሪኪናፋሶ በተካሄደ የማራቶን ውድድር በሴቶች አትሌት ዘይቱና ሙዲ 1ኛ በመግባት በበላይነት ማጠናቀቅ የቻለች ሲሆን፥ በወንዶች ደግሞ አትሌት ማላኒ ሀይማኖት 2ኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቋል።
እንዲሁም ባሳለፍነው ቅዳሜ እና እሁድ በተካሄዱ የግማሽ ማራቶን፣ 25 ኪሎ ሜትር፣ 10 ኪሎ ሜትር እና የ7 ነጥብ 5ኪሎ ሜትር ውድድሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል እንደቀናቸው ከአትሌቲክስ ፌደሬ ሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።