Fana: At a Speed of Life!

1 ነጥብ 4 ሚሊየን ዓመት ያስቆጠረ የጥንት ሰው መገልገያ መሳሪያ በኢትዮጵያ ተገኘ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የጥንት ሰው ዘር ከ1 ነጥብ 4 ሚሊየን ዓመት በፊት ከጉማሬ አጥንት ጠርቦ ሲገለገልበት የነበረ መሳሪያ ኢትዮጵያ ውስጥ በኮንሶ መካነ ቅርስ መገኘቱ ተረጋገጠ።

በኢትዮጵያውያንና ጃፓናውያን ተመራማሪዎች የተገኘው ይህ የጥንት ሰው መገልገያ መሳሪያ በዕድሜው ብዛትና በአሰራር ጥበቡ ከእስካሁን ግኝቶች ሁሉ የላቀ መሆኑ ተገልጿል።

በኮንሶ የፓሊዎ-አንትሮፖሎጂ የጥናት ቡድንና የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን እንዳስታወቀው ግኝቱ በአሜሪካ ሳይንስ አካዳሚ የጥናት መጽሄት ለህትመት በቅቷል።

አጥኚዎች እንደሚሉት የሰው ልጅ ከድንጋይ መሳሪያዎችን ሰርቶ መገልገል የጀመረው ከ2 ነጥብ 6 ሚሊየን ዓመት ቀደም ብሎ ነው።

በተለይም ከ1 ነጥብ 7 ሚሊየን እስከ 200 ሺህ ዓመታት ባሉት ጊዜያት “አሹሊያን” የተሰኙ የድንጋይ መገልገያ መሳሪያዎችን ይጠቀም ነበር።

“ሆሞ ኢሬክትስ” የተሰኘው ጥንታዊ የሰው ዘር ከ1 ነጥብ 7 ሚሊየን ዓመት በፊት ጀምሮ በኮንሶ መካነ ቅርስ መሳሪያዎችን ሰርቶ እንደተጠቀመ በጥናት የተረጋገጠ ሲሆን የአሁኑ ግኝትም ከጉማሬ የታፋ አጥንት የተሰራ ስለመሆኑ ተጠቁሟል።

ርዝመቱ 13 ሴንቲ ሜትር እንደሆነ የተገለጸው ይህ የመቁረጫ መሳሪያ የተገኘው በኢትዮጵያዊው ዶክተር ዮናስ በየነና በጃፓናዊው ዶክተር ጌን ሱዋ መሪነት በሁለቱ ሃገራት አጥኚዎች ትብብር በተዋቀረ የጥናት ቡድን ነው።

ግኝቱ እስካሁን በአፍሪካም በሆነ በአውሮፓ መካነ ቅርሶች በተደረጉ የአርኪዮሎጂ ጥናቶች ከተገኙ መሳሪያዎች ሁሉ በዕድሜው አንጋፋ፣ በጥሩ ሁኔታ ለዘመናት ተጠብቆ የቆየና የላቀ የአሰራር ጥበብ የታየበት እንደሆነም በመግለጫው ተጠቅሷል።

ጥንታዊ መሳሪያው ከጉማሬ የላይኛው የታፋ አጥንት ስለመሰራቱ ከሌሎች ትላልቅ እንስሳት ጋር በተደረጉ የንጽጽር ጥናቶች መረጋገጡ ተገልጿል።

በኮንሶ መካነ ቅርስ ከ2 ሚሊየን ዓመት በፊት ጀምሮ ጥንታዊ የሰው ዘር ቅሪቶች፣ በዓለማችን ረጅም ዕድሜ ያስቆጠሩ አሹሊያን የተሰኙ የድንጋይ መሳሪያዎችና የተለያዩ የእንስሳት ቅሪት አካላት ጥናቶች ተደርገዋል።

በዕድሜው 1 ነጥብ 4 ሚሊየን ዓመት ያስቆጠረው የአሁኑን ግኝት ጨምሮ በመካነ ቅርሱ የተገኙ በርካታ ሳይንሳዊ ግኝቶች ለህትመት መብቃታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.