አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከፖርቹጋል ውጪ ጉዳይና ትብብር ጋር በጋራ ለመስራት ተስማማ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከፖርቹጋል ውጪ ጉዳይና ትብብር ጋር በትምህርት ዲፕሎማሲ ረገድ አብሮ ለመስራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረመ።
ስምምነቱን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ ( ዶ/ር) እና በፖርቹጋል የውጭ ጉዳይና ትብብር ዋና ፀሀፊ ኑኖ ሳሞፒዮ ተፈራርመዋል።
ስምምነቱ በትምህርት ዲፕሎማሲው ዘርፈ ብዙ የትብብር መስኮችን ጨምሮ በዓለም በአራተኛ ደረጃ ብዙ ተናጋሪ ያለውን የፖርቹጋል ቋንቋን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለማስተማር የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ወቅት ፈረንሳይኛን ጨምሮ ሌሎች አለም አቀፍ ቋንቋዎችን በአጫጭር ኮርስ እንዲሁም በዲግሪ መርሃ ግብሮች በማስተማር ላይ እንደሚገኝ ከዩኒቨርሲቲው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡