ተግዳሮቶችን በመፍታት አፈጻጸም የሚያሻሽሉ እርምጃዎችን መተግበር ይገባል – ም/ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በመፍታት የበጀት ዓመቱን አፈጻጸም የሚያሻሽሉ እርምጃዎችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡
ከፌደራል ተቋማት አመራሮች ጋር የ2017 በጀት ዓመት የ100 ቀናት የሪፎርምና ዋና ዋና የኢኮኖሚ ትግበራዎች አፈጻጸም ግምገማ መካሔድ ጀምሯል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በመድረኩ እንዳሉት፤ በዋና ዋና የማክሮኢኮኖሚ ጉዳዮች አፈጻጸም መሻሻልና ለውጦች ተመዝግበዋል።
በተለይም በተደረጉ የታክስ ማሻሻያና አስተዳደር ማጠናከር ስራዎች የገቢ አሰባሰብ መሻሻሉንና የልማት ፋይናንስ ከብድርና ዕርዳታ ፍሰቱ ዕድገት ማሳየቱን ተናግረዋል።
ሪፎርሙ ሊያስከትል የሚችለውን ተጽዕኖ ለመቋቋም ውጤታማ የሆነ የመንግስት ወጪ አደራረግና አስተዳደር ስርዓት የተከተልንበት፣ የዕዳ ጫና የቀነሰበት፣ በውጤታማ መንገድ ባከናወነው ድርድር የመንግስት በጀት ላይ ብድር ለመክፈል የነበረውን ጫና ትርጉም ባለው ሁኔታ መቀነስ የቻልንበት ነበር ብለዋል።
የሪፎርሙ ዋነኛ ምሰሶ የሆነው የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓት በገበያ እንዲመራ በማድረግ በትይዩ የውጭ ምንዛሪ ገበያ መስፋፋት ምክንያት በየጊዜው ሲያጋጥም የነበረውን የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ፖሊሲ ችግሮች ማሻሻል የተቻለበት እንደነበርም ጠቁመዋል፡፡
በዚህም ምክንያት የውጭ ምንዛሪ ፍሰት ከተለያዩ ምንጮች በተለይም ከሐዋላ፣ ከወጪ ንግድ፣ ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መሻሻል ያሳየበት መሆኑን ጠቁመዋል።
የውጪ ምንዛሪ ሥርዓት ሪፎርም በኢኮኖሚ ውስጥ የነበሩ ሰፊ ውጤታማ ያልሆኑ አሰራሮች እንዲሻሻሉ፣ ብልሹ አሰራሮች እንዲወገዱና ውድድር እንዲበረታታ ማድረግ የተቻለበትና ይህንን ለማስቀጠል ጠንክረን መስራት ያለብን መሆኑን የተገነዘብንበት ወቅት ነው ብለዋል።
በፍሬህይዎት ሰፊው