‘MI6’ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ትብብር እንደሚጠናክር አረጋገጠ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሪታኒያ ‘ሴክሬት ኢንተለጀንስ ሰርቪስ (MI6)’ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያደርገውን ዘርፈ-ብዙ ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋገጠ፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ከፍተኛ አመራሮች እና የብሪታኒያ ‘ሴክሬት ኢንተለጀንስ ሰርቪስ (MI6)’ ልዑክ በተቋማት ደረጃ በሚከናወኑ በሁለትዮሽ፣ ቀጣናዊ፣ አኅጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
በዚሁ ወቅትም በቀጣናዊ፣ አኅጉራዊ፣ ዓለም አቃፋዊ ጉዳዮች በተለይም በቀይ ባሕር ወቅታዊ ሁኔታ፣ ሽብርተኝነትን፣ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችንና ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን በቅንጅት ለመከላከል በቀጣይ በሚደረጉ የመረጃ ልውውጥ ተግባራት ላይ ተወያይተዋል፡፡
የአገልግሎቱ ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ሲሳይ ቶላ እንዳሉት÷ ኢትዮጵያ የባሕር በር ተደራሽርነት እንዲኖራት የጀመረቸውን እንቅስቃሴ አንዳንድ አካላት ሆን ብለው ለሐሰት ፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ለመጠቀም እየሞከሩ ነው፡፡
ይህም ቀጣናው እንዳይረጋጋና እና ዘላቂ ሰላም እንዳይሰፍን አሉታዊ ተጽዕኖ እያበረከተ መሆኑን ጠቅሰው÷ የሁለቱ ተቋማት ግንኙነት በቀጣናው እያደገ ካለው አዲስ ሁኔታ ጋር እንዲጣጣም በጋራ መሥራት ይጠበቃል ብለዋል፡፡
በቀጣናው ያለው ያልተረጋጋ ሁኔታ ወደ ተረጋጋ ሰላማዊ ሁኔታ እንዲቀየር ኢትዮጵያ ወሳኝ ሚናዋን እየተወጣች እንደምትገኝ እና ይህንም አጠናክራ እንደምትቀጥል ተናግረዋል፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ፣ የቀጣናው ሀገራት በትብብር እንዲሠሩ የሚያበረታታ እንጂ÷ የልዩነት፣ የንትርክና የግጭት አጀንዳ መሆን እንደሌለበትም ነው ያስገነዘቡት፡፡
አገልግሎቱ ከቀጣናው ሀገራት እንዲሁም ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራትና ዓለምአቀፍ አቻ የመረጃ ተቋማት ጋር ጠንካራ የመረጃ ልውውጥ፣ የአጋርነትና የትብብር ሥራዎችን እየሠራ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
ከብሪታኒያ ‘ሴክሬት ኢንተለጀንስ ሰርቪስ (MI6)’ ጋር ያለውን ትብብርም ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገርና ማጠናከር ያስፈልጋል ማለታቸውን አገልግሎቱ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የላከው መረጃ አመላክቷል፡፡
የብሪታኒያ ‘ሴክሬት ኢንተለጀንስ ሰርቪስ (MI6)’ ኃላፊ ሪቻርድ ፒተር ሙር በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ ካላት ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ እና ተጽዕኖ ፈጣሪነት አንፃር በቀጣናዊ፣ አኅጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ትብብራቸው እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
በዚሁ መሠረት ተቋማቸው በደኅንነትና ጸጥታ ጉዳዮች ላይ እያደረገ ያለውን የመረጃ ልውውጥ ሥራ እንደሚቀጥል ነው ያመላከቱት፡፡
በተጨማሪም በቴክኖሎጂ እና አቅም ግንባታ መስኮች የጀመሯቸውን የትብብር እና አጋርነት ሥራዎች አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉ ተናግረዋል፡፡