Fana: At a Speed of Life!

ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ጫጩት ዶሮዎችን ለአርሶ አደሮች ሊያከፋፍል ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ  ጫጩት ዶሮዎችን ለአርሶ አደሮች ለማከፋፈል ማቀዱን አስታወቀ፡፡

የቅድመ ወላጅ ዶሮ እርባታ ፕሮጀክት የምርቃ መርሐ ግብር በሻሸመኔ ከተማ የተካሄደ ሲሆን÷ በመርሐ ግብሩ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ( ዶ/ር) እና የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አወሉ አብዲን ጨምሮ አምባሳደሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎችም ተገኝተዋል።

በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የኤልፎራ ድርጅት ሻሎ እርሻ ልማት ውስጥ የሚመረቱት ቅድመ ወላጅ ዶሮዎች በተወሰኑ አዳቃዮች ብቻ ይገኝ የነበረውን የዶሮ አቅርቦት በስፋት ለህብረተሰቡ ለማድረስ እየሰራ መሆኑን በድርጅቱ የኤልፎራ ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን አሰፋ ተናግረዋል።

በሚድሮክ ኢንቨስትመንት የኤልፎራ ቴክኒካል ባለሙያ ዶክተር ዳውድ ኢብራሂም ÷ከፈረጆቹ ሚያዝያ 2025 ጀምሮ በየሳምንቱ 15ሺህ ወላጅ ዶሮዎች ለአርሶ አደሮች ማከፋፈል እንጀምራለን ብለዋል።

የዶሮ ምርቱ ከውጭ አቅራቢዎች ወደ ሀገር የገባና ከአካባቢው አየር ንብረት ጋር ተስማሚ የሚሆኑ ዝርያዎች መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

ቅድመ ወላጅ ዶሮዎችን ወደ ሀገር አስገብቶ ማዳቀል መቻል ሀገር ታወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ ማስቀረት የሚያስችል መሆኑም ተገልጿል።

በመቅደስ አስፋው እና ጥላሁን ይልማ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.