የወባ ስርጭትን ለመከላከል የተቀናጀ ስራ ሊሰራ ይገባል- ዶ/ር መቅደስ ዳባ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የወባ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጣር የተቀናጀ ስራ ሊሰራ ይገባል ሲሉ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ፡፡
የወባ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጣር እየተከናወነ ያለውን ስራ በሚመለከት በተደረገው የግምገማ መድረክ ዶክተር መቅደስ ዳባ በበይነ መረብ ባስተላለፉት መልዕክት÷ የወባ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጣር የተቀናጀ ስራ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
ሚኒስቴሩ ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ማስተባበሪያ ማዕከል፣ ከክልል ጤና ቢሮዎችና ክላስተሮች ጋር ስርጭቱን ከመከላከልና ከመቆጣጣር ረገድ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን በመገምገም ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት እየሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
ይሁን እንጂ ከክረምት መውጣት ጋር ተያይዞ የወባ በሽታ ስርጭት እየጨመረ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን÷ስርጭቱን ለመግታት በየደረጃው ያለው አመራር፣ የጤና ባለሙያና ባለድርሻ አካላት በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ መገለፁን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
በመድረኩ የክልል ጤና ቢሮ ሀላፊዎች÷ የወባ በሽታ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየተሰሩ ያሉ ስራዎች፣ የታዩ ክፍተቶች፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች፣ የተወሰዱ እርምጃዎችንና በቀጣይ መሰራት የሚገባቸው የትኩረት አቅጣጫዎች በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል፡፡