በአዲሱ የ2024/25 ዓመት የአፈር ማዳበሪያ ዝውውር ላይ የቅድመ-ዝግጅት ውይይት ተደረገ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በጂቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዛሬ ከኦፕሬሽን ኮሚቴ ጋር በመሆን በአዲሱ የ2024/25 ዓመት የአፈር ማዳበሪያ ዝውውር ላይ የቅድመ-ዝግጅት ውይይት አድርጓል።
የጂቡቲ ማዳበሪያ ኦፕሬሽን ኮሚቴ በ2023/24 የስራ ዘመን ከጂቡቲ ወደብ ወደ ኢትዮጵያ የሚጓዘውን የአፈር ማዳበሪያ ኦፕሬሽን በቅርበት በመከታተል ከጂቡቲ ባለድርሻና ኢትዮጵያ ካለው አብይ ኮሚቴ ጋር ተቀናጀቶ በተሳካ ሁኔታ ማጠናቀቁን አንስቷል።
በዚህ ሂደት ውስጥ መሻሻል ያለባቸውን እና ለቀጣይ የ2024/25 ዓመት የአፈር ማዳበሪያ ዝውውር በትኩረት መታየት ያለባቸው ጉዳዮችን በመዳሰስ ኮሚቴው በስፋት ተወያይቷል።
አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ በዚህ ወቅት ፥ ዘንድሮ ወደ ሀገር ቤት እንዲገባ የታቀደው የአፈር ማዳበሪያ መጠን ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር ጭማሪ ያሳያል ብለዋል፡፡
በዚህም የተጀመሩ የክትትል ስራዎችን በማጠናከር በጂቡቲ የሚደረጉ የቅድመ-ዝግጅት ስራዎች እንዲጠናከሩ አሳስበዋል።
በኢትዮጵያ ያለው ዐብይ ኮሚቴም ተመሳሳይ ጥረት ሊያደርግ እንደሚገባ መግለጻቸውን ከኤምባሲው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።