የልማት ዕቅዶችና አቅጣጫዎች እንዲሳኩ አመራሩ ቁርጠኛ ሆኖ ሊሰራ ይገባል – አቶ ሽመልስ አብዲሳ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በመንግስት የተቀረፁ ኢኒሼቲቮች፣ የልማት ዕቅዶች እና አቅጣጫዎች ግባቸውን እንዲመቱ አመራሩ ቁርጠኛ ሆኖ ሊሰራ ይገባል ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።
የክልሉ የ2017 በጀት ዓመት የመጀሪያ ሩብ የመንግስት እና የፓርቲ የስራ አፈፃፀም ግምገማ መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ሲሆን፤ በመድረኩ በሶስት ቀናት ቆይታው የመንግስት እና የፓርቲ ዕቅድ አፈፃፀም ላይ ይወያያል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ክልሉ በሁሉም ዘርፎች የያዛቸው ውጥኖች ውጤታማ እንዲሆኑ አመራሩ ቁርጠኛ ሆኖ መስራት እንዳለበት አሳስበዋል።
በዚህም አመራሩ ድህነትን በመቅረፍ እና የዜጎችን ሕይወት በሚያሻሽሉ ተግባራት ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
በክልሉ ማሕበረሰባዊ ጠቀሜታቸው ከፍ ያሉ ስራዎች ተግባራዊ እየተደረጉ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ከጥራት አንፃር ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ አመላክተዋል።
የማህበረሰቡን ችግር ለመፍታት ተግባራዊ ምላሽ መስጠት፣ ያሉ አቅሞችን አስተባብሮ መጠቀም እና ገቢን ማሳዳገ ላይ ቁርጠኛ መሆን እንደሚገባ ጠቁመዋል።
እንደ ክልል የተቀረፁ ኢኒሼቲቮች፣ የልማት ዕቅዶች እና የተቀመጡ አቅጣጫዎች ተግባራዊነታቸውን መከታተል እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በወንድሙ አዱኛ