ሚዲያዎች ኢትዮጵያዊያንን አንድ በሚያደርጉ ትርክቶች ላይ ትኩረት አድርገው ሊሰሩ ይገባል ተባለ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) “የሚዲያ ሚና ለትርክትና ሀገረ መንግሥት ግንባታ” በሚል መሪ ሃሳብ በመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አዘጋጅነት ለሚዲያ አመራሮችና ባለሙያዎች የሚሰጥ ስልጠና ዛሬ ተጀምሯል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስተሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ዲያቆን ዳንኤል ክብረት “ሚዲያ ለብሔራዊ ትርክትና ሀገረ መንግሥት ግንባታ” በሚል ርዕስ ላይ ገለጻ አድርገዋል፡፡
በገለጻቸውም ሚዲያዎች ኢትዮጵያዊያንን አንድ በሚያደርጉን ትርክቶች ላይ ትኩረት አድርገው መሥራት እንደሚጠበቅባቸውና ሀገር የሚገነባው በአዎንታዊ ትርክቶች መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሥራ ትርክትን እንደሚቀይር የተናገሩት አማካሪ ሚኒስትሩ÷ ባዶ ትርክ እንደማይጸናና ተግባራዊ ሥራ ሲሰራ ትርክቶች ይለወጣሉ ብለዋል።
ትላንት የነበረው የአባይ ውሃ ዛሬ ሕዳሴ ግድብን ሰርተን ስናጠናቅቅ ትርክቱ ተቀይሯል በማለት ሥራ ተግባርን እንደሚቀር አመላክተዋል፡፡
ትርክቶች አካታች መሆን እንዳለባቸውና ልሂቃን የሚገቡ ትርክቶች መቃናት እንዳለባቸው ጠቁመው÷ ትርክት ለነገ ሲባል የትላንቱን የሚተወውን ትተን፣ የዛሬንም ይቅር ብለን ነገን የምንገነባበት ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡
ትርክት የአብሮነት ታሪካዊ መሰረት እንደሆነ፤ ሰዎች ከየት ተነስተው እና ወደየት እንደሚሄዱ እና የት እንደሚደርሱ የሚመለከቱበት መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
ለመገናኛ ብዙሃን “ሚዲያ ለብሔራዊ ትክርክትና ለሀገረ መንግሥት ግንባታ” በሚል ርዕስ የተዘጋጀው ስልጠና ለሶስት ቀናት እንደሚሰጥ መገለጹንም የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መረጃ ያመላክታል፡፡