ሃሰተኛ የውጭ ሀገር ሕክምና ሪፈር ሰነድ በማዘጋጀት የተከሰሰው የሥነ-ምግባር መኮንን እንዲከላከል ብይን ተሰጠ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ሃሰተኛ የውጭ ሀገር ሕክምና የሪፈር ሰነድ አዘጋጅቶ በመስጠት ሙስና ወንጀል የተከሰሰው የሥነ-ምግባር መኮንን እንዲከላከል ብይን ተሰጠ።
በተከሰሰበት የሙስና ወንጀል ክስ ላይ በዐቃቤ ሕግ የቀረበበትን ማስረጃ መርምሮ ተከሳሹ እንዲከላከል ብይን የሰጠው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።
ይህ እንዲከላከል ብይን የተሰጠበት ተከሳሽ በአዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ውስጥ የስነ ምግባር መኮንን የነበረው ጌቱ ደጀኔ የተባለ ግለሰብ ነው።
የፍትሕ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በተከሳሹ ላይ የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀፅ 23 ንዑስ ቁጥር (1) U፣ (2)እና (3) ስር እንዲሁም አንቀፅ 32 ንዑስ ቁጥር (2) ስር የተመለከተውን ድንጋጌ ተላልፏል የሚል ተደራራቢ ክሶችን አቅርቦበት ነበር።
በዚህ በቀረበበት ዝርዝር ክስ ላይ እንደተመላከተው ተከሳሽ በአዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ውስጥ የሥነ-ምግባር መኮንን ሆኖ በሚያገለግልበት ጊዜ ያልተገባ ጥቅምን ወይም መሻሻልን ለማግኘት በማሰብ ካልተያዘው ግብረአበሩ አባይ ገ/ስላሴ ከከሚባል ግለሰብ ጋር በመሆን በጥቅምት ወር 2015 ዓ.ም እራሳቸውን በጥቁር አንበሳ አጠቃላይ ሆስፒታል ውስጥ የሚሰሩ የሕክምና ባለሙያዎች አስመስለው ግለሰቦችን በመቅረብና በመተዋወቅ የማታለል ተግባር ይፈጽሙ እንደነበር ዐቃቤ ሕግ በክሱ ዝርዝር ላይ ጠቅሷል።
በዚህ መልኩ ተከሳሹ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች የሆኑ ሁለት ግለሰቦችን በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ውስጥ “ወደ ውጭ ሀገር እንድትሄዱ እናዳርጋለን “በሚል ለፕሮሰስ ማስጀማሪያ ተከሳሹ ከሁለት የዐቃቤ ሕግ ምስክር ከሆኑ ግለሰቦች 200 ሺህ ብር በንግድ ባንክ በከፈተው ሒሳቡ ገንዘብ የተቀበለ መሆኑ በክሱ ዝርዝር ላይ ተገልጿል።
ከንዘቡን ከተቀበለ በኃላ በድጋሚ በየካቲት ወር 2015 ዓ.ም 1ኛ የዐቃቤ ሕግ ምስክርን በአካል በማግኘት “አንተን ከአቅም በላይ የሆነ ከባድ ሕመም ታማሚ እንደሆንክ አድርጌ እጽፋለሁ በማለት” እንዲሁም 2ኛ የዐቃቤ ሕግ ምስክር ወንድምን ደግሞ “አስታመሚ በመሆን ወደ ውጭ ሀገር እንድትሄዱ አደርጋለሁ “በማለት የተዘጋጀ የልብ ሕመም ታማሚ እንደሆነ እና ወደ ውጭ ሄዶ መታከም እንዳለበት የሚጠቅስ የጥቁር አንበሳ ስፕሻላይዝድ ሆስፒታል የሕክምና ቦርድ የተሰጠ” እንድታውቁት” የሚል ሀሰተኛ ሰነድ በየካቲት12 ቀን 2015 ዓ.ም ለ1ኛ የዐቃቤ ሕግ ምስክር በመስጠት ገንዘብ የወሰደ መሆኑ በክሱ ተጠቅሶ በከባድ የማታለል ሙስና ወንጀል ተከሷል።
በሁለተኛ ክስ ደግሞ ተከሳሹ ሀሰተኛ ሰነዶችን ማዘጋጀት ወንጀል ተጠርጥሮ የካቲት 10 ቀን 2016 ዓ.ም በፌደራል ፖሊስ አባላት በጥቁር አንበሳ ስፕሻላይዝድ ሆስፒታል በሥነ ምግባር መኮንንነት ብቻውን ከሚገለገልበት ቢሮ ውስጥ በተደረገ ብርበራ በ16 ግለሰቦች ስም እና ፎቶ ሀሰተኛ ሰነዶች መገኘታቸው ተገልጿል።
ይህም ሰነድ እና አንድ ግለሰብ ከባድ ሕመም ስለገጠማቸው ወደ ውጭ ሀገር ሄደው እንዲታከሙ የውጭ ምንዛሪ እንዲሰጣቸው እናሳስባለን በሚል ከጤና ሚኒስቴር ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዓለም አቀፍ ግንኙነት በተለያየ ቀን የተፃፈ ብዛታቸው 15 የሆኑ ሀሰተኛ ሰነዶችን እና የጥቁር አንበሳ ስፕሻላይዝድ ሆስፒታል ቦርድ ወደ ውጭ ሄደው እንድትታከሙ የወሰነ ስለመሆኑ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንዲያውቀው በሚል ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሜዲካል ፋካሊቲ በተለያየ ቀን እና ቁጥር የተፃፈ ብዛታቸው10 የሆኑ ሀሰተኛ የቦርድ ውሳኔ አባሪ ሰነዶችን በቢሮው ውስጥ ካለ መሳቢያ ውስጥ አስቀምጦ የተገኘ መሆኑ ተጠቅሷል።
በተጨማሪም በተከሳሹ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሰርጀሪ ሜዲካል ፋካሊቲ በሚል ስም የተቀረፀ ክብ ማሕተም፣ ጤና ሚኒስቴር -ኢትዮጵያ የዜጎች ጤና ለሀገር ብልፅግና የሚል ስም የተቀረፀ ባለ ሶስት ማዕዘን ማሕተም እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምግብና መድሃኒት ጤና እንክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለስልጣን በሚል ተቋም ስም የተቀረፀ ክብ ማሕተም አስቀርፆ በቢሮው ካለ መሳቢያ ውስጥ አስቀምጦ የተገኘ በመሆኑ በክሱ ተጠቅሶ በፈፀመው የሃሰት ሥራ ለማስፈፀም የሚያገለግሉ መሳሪያዎችንና መስሪያዎችን ይዞ እና አስቀምጦ መገኘት ወንጀል ተከሷል፡፡
ተከሳሹ በዚህ መልኩ የቀረበበትን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸሙን ጠቅሶ የሰጠውን የእምነት ክህደት ቃል ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ የምስክር ቃልና የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቧል።
ፍርድ ቤቱም በተከሳሹ ላይ የቀረቡ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃዎችን መርምሮ በተለያዩ የሕክምና ተቋማት ስም የተቀረጹ ቲተርና ማሕተሞኝ፣የሕክምና ሰነዶች ሀሰተኛ መሆናቸው መረጋገጡን ጠቅሶ ተከሳሹ በተከሰሰባቸው 3 ክሶች ሊከላከል ይገባል በማለት በሙሉ ድምጽ ብይን ሰጥቷል።
ተከሳሹ የመከላከያ ማስረጃ ካለው ለመጠባበቅ ለሕዳር 23 ቀን 2017 ዓ.ም ተቀጥሯል።
በታሪክ አዱኛ