በሕይወት ያለችን ግለሰብ እንደሞተች በማስመሰል በሐሰተኛ የወራሽነት ሠነድ ከ1 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር በላይ የወሰዱ ግለሰቦች በጽኑ እስራት ተቀጡ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በሕይወት ያለች ግለሰብን ሞታለች በማለት የቀብር ሥነ-ሥርዓት የተፈጸመ በማስመሰል በሐሰተኛ የወራሽነት ሠነድ ከ1 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር በላይ ገንዘብ የወሰዱ ግለሰቦች በጽኑ እስራት ተቀጡ፡፡
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ÷ በሕይወት ያለች ግለሰብን ሞታለች በማለት የቀብር ሥነ-ሥርዓት የተፈጸመ በማስመሰል ሐሰተኛ የወራሽነት ሠነዶችን በመጠቀም ከ1 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር በላይ በማታለል ከባንክ ወስደዋል በተባሉ ተከሳሾች የቀረቡ ማስረጃዎችን መርምሮና አመዛዝኖ በጽኑ እስራትና በገንዘብ እንዲቀጡ ወስኗል።
የፍትሕ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ሳሙኤል አብረሃም ዋቅጅራ እና ሩት አብርሃም ዋቅጅራ በተባሉ ሁለት ግለሰቦችላይ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀፅ 32(1)(ሀ) እና የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀፅ 32(2) እና 32(3) ላይ የተመለከተውን መተላለፍ የሚል ክስ አቅርቦባቸው ነበር።
ተከሳሾች የማይገባ ብልጽግና ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ ጥቅምት 28 ቀን 2015 ዓ.ም ለቡራዩ ክፍለ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በሕይወት ያለችው እና በአሜሪካ ሀገር የምትኖረው ሰላማዊት ይልማ ኃይሉ “እናታችን ናት፤ የአዳማ ከተማ ነዋሪ ነበረች ሰኔ 13 ቀን 2014 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታ ሰኔ 14 ቀን 2014 ዓ.ም አዳማ ከተማ ቦኩ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ሥርዓተ-ቀብሯ የተፈጸመ ሲሆን÷ በሟች ስም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሂሳብ ቁጥር የሚገኘው ብር ወራሽ መሆናችን ተረጋግጦ ሂሳቡን ለማንቀሳቀስ እንድንችል እንዲወሰንል” በማለት የወራሽነት አቤቱታ አቅርበዋል፡፡
1ኛ ተከሳሽ ሐሰተኛ የሆነ ከሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ያልተሰጠ የመከላከያ አባልነት ገላጭ መታወቂያ በሠነድ ማስረጃነት በማያያዝ እና በሕይወት ያለችውን ተበዳይ ሞታለች በማለት አሳሳች ነገር መግለጻቸው፤ የቡራዩ ክፍለ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትም ሕዳር 22 ቀን 2015 ዓ.ም ባስቻለው ችሎት በቀረበው አቤቱታ መሰረት ተከሳሾች ወራሽ መሆናቸውን በመወሰን በግል ተበዳይዋ ሂሳብ ውስጥ የሚገኘውን የወራሽነት ድርሻቸው መሆኑን ገልጾ ትዕዛዝ መስጠቱ በክሱ ተጠቅሷል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ከቡራዩ ክፍለ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በተሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ሕዳር 28 ቀን 2015 ዓ.ም ከግል ተበዳይ ሂሳብ ውስጥ ተቀናሽ በማድረግ በ1ኛ እና በ2ኛ ተከሳሾች ስም በተከፈተ ሂሳብ ለእያንዳንዳቸው 922 ሺህ 319 ብር ማስተላለፉ፣ ጥቅም ማግኘታቸውና በዚሁ ልክ ጉዳት ማድረሳቸው ተጠቅሶ በሕዝብ አሥተዳደር ወይም በሕዝብ አገልግሎት ላይ በሚፈጸመው ከባድ አታላይነት የሙስና ወንጀል ተከሰዋል።
ከሁለቱ ተከሳሾች መካከል ሩት የተባለችው ሁለተኛ ተከሳሽ ያልተያዘች መሆኑን ተከትሎ በሌለችበት ጉዳይዋ የታየ ሲሆን÷ አንደኛ ተከሳሽ ግን በቁጥጥር ስር ውሎ ማረሚያ ቤት ሆኖ ጉዳዩን ሲከታተል ቆይቷል።
1ኛ ተከሳሽ የክሱ ዝርዝር ከደረሰው በኋላ በክሱ ዝርዝር ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸሙን ጠቅሶ የዕምነት ክህደት ቃሉን ሰጥቷል፡፡
ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ ለወንጀሉ መፈጸም ያስረዱልኛል ያላቸውን ምስክሮችን አቅርቦ የምስክር ቃላቸውን አሰምቷል።
ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ሕግን ምስክር ቃል መርምሮ አንደኛ ተከሳሽ በተከሰሰበት ድንጋጌ ስር ማለትም በሙስና አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀፅ 32(2) እና 32(3) ስር እንዲከላከል ያለ ሲሆን÷ ሁለተኛ ተከሳሽን በተመሳሳይ በተከሰሰችበት ድንጋጌ ስር የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎባታል።
አንደኛ ተከሳሽ የተለያዩ የመከላከያ ማስረጃዎችን ቢያቀርብም÷ የዐቃቤ ሕግን ማስረጃ መከላከል (ማስተባበል) አለመቻሉን መዝገቡን በሚመለከቱት ዳኛ ተገልጿል።
በተለይም ሞታለች የተባለችው ግለሰብ በሕይወት ያለች መሆኗን፤ ሞታለች በተባለች ግለሰብ በባንክ ሂሳብ ውስጥ የነበረ ገንዘብን በሐሰተኛ የወራሽነት ማስረጃ አቅርበው ፍርድ ቤቱን በማሳሳት እንዲሰጣቸው ባደረጉት የወራሽነት ትዕዛዝ መሰረት ከንግድ ባንክ 922 ሺህ 319 ብር ከ98 ሳንቲም ገንዘብ እያንዳንዳቸው የወሰዱና ጥቅም ያገኙ መሆኑ መረጋገጡን መዝገቡን የተመለከቱት ዳኛ አብራርተዋል።
በዚህም ተከሳሹ በተከሰሰበት ድንጋጌ ስር የወንጀል ድርጊቱን መፈጸሙ መረጋገጡ ተጠቅሶ የጥፋተኝነት ፍርድ በሙሉ ድምጽ ተሰጥቷል።
ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየት መርምሮ አንደኛ ተከሳሽ ያቀረበውን የቅጣት ማቅለያ አስተያየቶች በመያዝ በ4 ዓመት ጽኑ እስራትና 8 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ የተወሰነ ሲሆን÷ ሁለተኛ ተከሳሽን ደግሞ በ6 ዓመት ጽኑ እስራትና 40 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንድትቀጣ ተወስኗል።
በታሪክ አዱኛ