ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን የዲፕሎማሲ ሚና በማላቅ በትብብር እንደምትሠራ ተመላከተ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በቀጣናው፣ በአኅጉሩ እና ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን የዲፕሎማሲ ሚና በማላቅ በትብብር መንፈስ እንደምትሠራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ሚኒስትሩ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማቱ የሥራ ኃላፊዎች እና ሠራተኞች ጋር የሥራ ገለፃና ትውውቅ አድርገዋል።
ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት ተቋማቸው የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ሊከተላቸው የሚገቡ የትኩረት አቅጣጫዎችን አብራርተዋል፡፡
ተለዋዋጭ ለሆኑት ቀጣናዊና ዓለምአቀፋዊ ክስተቶች በእውቀት እና በምርምር የታገዘ የዲፕሎማሲ ሥራ ያስፈልጋል ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡
ኢትዮጵያ ረጅም ዘመን ያስቆጠረ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ታሪክ እንዳላት ገልጸው÷ በቀጣናው እና በአኅጉር ደረጃ በሚኖራት ሚና ብሎም ተፅዕኖ ፈጣሪነት ዲፕሎማሲዋን በይበልጥ በማላቅ መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡
በዓለምአቀፍ መድረክ ኢትዮጵያ በሚኖራት የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዎች የጋራ ጥቅምን ማዕከል ያደረገ ትብብርን ማሳደግ እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በበኩላቸው÷ የተጀመሩ የውጭ ግንኙነት የለውጥ ተግባራትን በማጠናከር ለጋራ ግብ እና ለውጥ እንደሚሠራ ተናግረዋል።