በሀሰተኛ ቼክና ፊርማ ከንግድ ባንክ 89 ሚሊየን ብር ሊያወጣ ሲል ተይዟል የተባለው ግለሰብ ላይ ክስ ተመሰረተ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ተመሳስሎ በተሰራ ሀሰተኛ ቼክና ፊርማ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 89 ሚሊየን ብር ሊያወጣ ሲል በባንኩ ሰራተኞች ማጣሪያ በክትትል ተይዟል የተባለው ግለሰብ ላይ ክስ ተመስርቷል፡፡
ክሱ የተመሰረተው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ድሬደዋ ምድብ ወንጀል ችሎት ነው።
በፍትሕ ሚኒስቴር ድሬደዋ ቅርጫፍ ጽ/ቤት የፌደራል ዐቃቤ ሕግ በተከሳሹ ላይ የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 23 ስር የተመለከተውን ድኔጋጌ መተላለፍ የሚል ክስ አቅርቦበታል።
ይህ ክስ የቀረበበት ተከሳሽ የአዲስ አበባ ከተማ የጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ኗሪ ነው የተባለው ሐጂ ረሺድ ሺፋ ሠዒድ ይባላል።
ዐቃቤ ሕግ በተከሳሹ ላይ ባቀረበው ክስ ላይ እንደተመላከተው ተከሳሽ የሌላውን ሰው መብት ወይም ጥቅም ለመጉዳት፣ ለራሱ ወይም ለሌላ ሰው ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለማስገኝት በማሰብ ሚያዝያ 11 ቀን 2016 ዓ.ም ከቀኑ 8፡30 ገደማ በድሬዳዋ ከተማ ቀበሌ 6 በሚገኘው በንግድ ባንክ ፈረስ መጋላ ቅርንጫፍ በመቅረብ ከአየር ጤና ቅርንጫፍ የሂሳብ ቁጥር የተጠቀሰበት ለገብረግዚ ጸሀዬ እና ሰለሞን ገብሬ በሚል ተመሳስሎ በተሰራ እና በተፈረመ የቼክ ለክፍያ ይዞ መቅረቡ በክሱ ተመላክቷል።
ተከሳሹ በአንደኛው ቼክ ላይ 45 ሚሊየን ብር እንዲሁም በሌላኛው በቼክ ቁጥር ደግሞ 44 ሚሊየን ብር በጥሬ ገንዘብ ለክፍያ የታዘዘ በማስመሰል በድምሩ 89 ሚሊየን ብር የሚያወጡ ቼኮችን ይዞ በባንኩ በመቅረብ ክፍያ እንዲፈጸምለት መጠየቁም ተጠቅሷል፡፡
የባንኩ ሰራተኞች የቼኩን ትክክለኛነት በማጣራት ላይ እያሉ ወጥቶ የተሰወረ ሲሆን÷በተደረገ ጥብቅ ክትትል በመስከረም 10 ቀን 2017 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ በቁጥጥር ስር የዋለ መሆኑ ተጠቅሶ መንግስታዊ ወይም ህዝባዊ ድርጅት ሠነዶችን አስመስሎ ማዘጋጀት፣ ወደ ሀሰት መለወጥ ወይም በሀሰተኛ ሰነድ መገልገል ከባድ ሙስና ወንጀል ተከሷል፡፡
ዐቃቤ ሕግ በክስ ዝርዝሩ ላይ የ3 የሰው ምስክሮችና በባንኩ ቀርቧል የተባሉ ቼክና ለክፍያ ተሞልተዋል የተባሉ ፎርሞችን በሰነድ ማስረጃነት አያይዞ አቅርቧል።
ተከሳሹ የክስ ዝርዝሩ ከደረሰው በኋላ ክሱ እንዲሻሻልለት የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ በጽሑፍ አቅርቧል።
ፍርድ ቤቱም ተከሳሹ ያቀረበውን የክስ መቃወሚያና የዐቃቤ ሕግ መልስ መርምሮ ብይን ለመስጠት ለጥቅምት 26 ቀን 2017 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል
በታሪክ አዱኛ