Fana: At a Speed of Life!

የኮሪደር ልማት ማለት ኢትዮጵያን የሚመጥን ከተማ መገንባት ነው- ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኮሪደር ልማት ማለት ኢትዮጵያን የሚመጥን ከተማ መገንባት ማለት ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስገነዘቡ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኮሪደር ልማትን በተመለከተ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ÷ ኮሪደር ልማት ከከተሜነት እድገት ጋር የተሳሳረ ልማት ነው፤ ከተማ አደገ ማለትም የሀገር ኢኮኖሚ አደገ ማለት ነው ብለዋል፡፡

በኮሪደር ልማት ሰፋፊ መንገድ ከመሥራት ባለፈ ታዳጊዎች ኳስ የሚጫወቱባቸው የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እና የእግረኛ መንገዶች መሠራታቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

ፓርኮች በየቦታው እየተገነቡ መሆኑን ገልጸው÷ ይህም ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ፍትሐዊ ልማት ለዜጎቻችን የቀረበበት ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡

የኮሪደር ልማት ሥራው በዓለም አቀፍ ደረጃ አድናቆትን ያተረፍንበት በመሆኑ በቀላሉ ሊታይ አይገባም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ አሁን ላይ በከተሞች ከሚሠሩ የኮሪደር ልማት ሥራዎች ባሻገር የገጠር ኮሪደር ልማት ሥራ መጀመሩን አስረድተዋል፡፡

የኮሪደር ልማቱን ተግባራዊ ለማድረግ ሕብረተሰቡን ማወያየት፣ ካሳ መክፈልና መሰል ጉዳዮች ላይ መሠራት እንዳለበትም አመላክተዋል፡፡

በአመለወርቅ ደምሰው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.