Fana: At a Speed of Life!

በሚቀጥሉት ቀናት በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑ አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በቀጣዮቹ 10 ቀናት በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑ አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

በሌላ በኩል በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የበጋው ደረቅ፣ ፀሐያማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ እንደሚስተዋል ኢንስቲትዩቱ ገልጿል፡፡

በሚቀጥሉት ቀናት ዝናብ ሰጭ የአየር ሁኔታ ክስተቶች በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት የደቡብ እና ደቡብ ምስራቅ እንዲሁም በምዕራብና በደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ የተሻለ ገጽታ እንደሚኖራቸው ትንበያው አመላክቷል፡፡

በአጠቃላይ በሚቀጥሉት 10 ቀናት በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት ከኦሮሚያ ክልል ባሌ እና ምስራቅ ባሌ፣ ጉጂና ምዕራብ ጉጂ፣ ቦረና እና ምስራቅ ቦረና ዞኖች፤ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ፣ ወላይታ፣ ኮንሶ፣ በጌዲኦ፣ ባስኬቶ በጎፋ፣ ደቡብ ኦሞ፤ አሌ፣ በአማሮ እና ቡርጂ ዞኖች ከቀላል መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ፡፡

በተጨማሪም ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ኮንታ እና ምዕራብ ኦሞ ዞኖች፤ ከሶማሌ ክልል ዳዋ፣ ሊበን፣ አፍዴር፣ ሸበል፣ ኖጎብ፣ ቆራሂ፣ ዶሎ ፋፋን፣ ኤረር እና ጃረር፤ እንዲሁም ሀረሪ እና ድሬዳዋ ላይ በብዙ ቦታዎቻቸው ላይ ከቀላል መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ መረጃው አመላክቷል፡፡

እንዲሁም ከክረምት ጀምሮ ዝናብ እያገኙ ባሉት አካባቢዎች ማለትም በምስራቅ ወለጋ፣ ሆሮጉዱሩ ወለጋ፣ አርሲ እና ምዕራብ አርሲ፤ምስራቅ እና ምዕራብ ሀረርጌ፣ መተከል፣ አሶሳ፣ ካማሺ እና የማኦኮሞ ልዩ ዞን፤ የኢታንግ ልዩ ዞን፣ ኑዌር እና አኝዋክ ዞኖች በብዙ ቦታዎቻቸው ላይ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ተተንብይዋል፡፡

በሌላ በኩል አልፎ አልፎ ከሚጠናከሩት የአየር ሁኔታ ክስተቶች ላይ በመነሳት ከአማራ ክልል ምዕራብ፤ ሰሜን፣ ማዕከላዊና ደቡብ ጎንደር፤ ምስራቅ፤ ምዕራብ እና ሰሜን ጎጃም፤ አዊ ዞኖች እና ባህርዳር ዙሪያ፤ ሰሜንና ደቡብ ወሎ፣ ዋህግምራ፤ ሰሜን ሸዋ፣ እና የኦሮሞ ብሄረሰብ ልዩ ዞን፤ ከትግራይ ክልል የሰሜን ምዕራብ፤የምዕራብ፣ የደቡብና የደቡብ ምስራቅና ዞኖች፤ ከአፋር ክልል ፋንቲ፤ ማሂ፣ ሃሪ፣ እና ጋቢ ዞኖች፤ ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅ፣ ምዕራብ፣ ደቡብ ምዕራብ እና ሰሜን ሸዋ (ሰላሌ)፤ አዲስ አበባ፤ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች በተለይም በመጀመሪያዎቹ ቀናቶች ላይ ወቅቱን ያልጠበቀ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት መረጃ ጠቁሟል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.