የኦፌኮ አመራራር አቶ በቀለ ገርባና አቶ ጃዋር መሃመድ ፍርድ ቤት ቀረቡ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአርቲስት ሀጫሉ ግድያን ተከትሎ አስክሬን በመቀማት እና ሁከት በመፍጠር ወንጀል የተጠረጠሩት አቶ ጃዋር መሃመድና አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ ሌሎች ግለሰቦች ፍርድ ቤት ቀርበዋል።
የኦፌኮ አባል የሆኑት አቶ ጃዋር መሀመድ እና አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ 21 ተጠርጣሪዎች በፌደራል ልደታ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ተረኛ ችሎት ቀርበው መርማሪ ፖሊስ የሰራውን የምርመራ ስራ ይፋ አድርጓል።
አቶ ጃዋር መሀመድ በተጠረጠሩበት ሁከት እና አመፅ እንዲፈጠር ብሄርን ከብሄር፣ ሀይማኖትን ከሀይማኖት ግጭት እንዲፈጠር በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ዞኖች ትእዛዝ በመስጠት በንብረት እና በሰው ህይዎት ላይ ጉዳት እንዲደርስ ማድረግ ወንጀል መፈፀማቸውን የሚያረጋግጥ በርካታ የሰው እና የሰነድ ማስረጃ መሰብሰቡን መርማሪ ፖሊስ ለችሎቱ አስረድቷል።
አቶ ጃዋር በሚዲያቸው (ኦ ኤም ኤን) አመፅ በመቀስቀስም በአዲስ አበባ ብቻ ከ200 ሚሊየን ብር በላይ ንብረት መውደሙንም መርማሪ ፖሊስ ጠቅሷል።
መርማሪ ፖሊስ በግለሰቡ መኖሪያ ቤት አገኘሁት ባለው በርካታ የጦር መሳሪያ እና የሳተላይት መቆጣጠሪያን ጨምሮ ሌሎች የተገኙ መሳሪያዎች ላይ በፎረንሲክ ምርመራ እየተደረገባቸው ነው ብሏል።
በርካታ የሰውና የሰነድ ማሠረጃዎን መሰብሰቡን በመጥቀስም ፖሊስ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀን ይሰጠኝ ሲልም ጠይቋል።
አቶ ጃዋር በበኩላቸው እኔ በዚህ ድርጊት ተሳትፎ ልወነጀል አይገባም በማለት ይህ የፖለቲካ ጉዳይ ነው ተነጋግሮ በውይይት መፍታት ሲቻል በዚህ መልኩ መወንጀሌ ተገቢነት የለውም የሚሉትን ጨምሮ ሌሎች መቃወሚያዎችን አቅርበዋል፡፡
በጠበቃቸው በኩልም በማረሚያ ቤት ያለው አያያዝ ይሰተካከልልኝ ሲሉም አቤቱታ አቅርበዋል።
ግራ ቀኙን ያዳመጠው ፍርድ ቤትም አያያዛቸውን በተመለከተ ፖሊስ ማስተካከያ እንዲያድርግ ትእዛዝ ሰጥቷል።
ለተጨማሪ ምርመራም ፖሊስ የጠየቀውን 14 ቀን በመፍቀድም ለሀምሌ 22 ቀን 2012 አመተ ምህረት ውጤቱን ለመጠባበቅ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በሁለተኛ መዝገብ የቀረቡት የአቶ ጃዋር ጠባቂ ናቸው የተባሉ 9 ተጠርጣሪዎች ላይም መርማሪ ፖሊስ ሰኔ 23 ቀን በእጃቸው ላይ 10 ክላሽ መሳሪያ፣ 1 ችች ጠመንጃ፣ 11 ሽጉጥ እና 9 የሬዲዮ መገናኛ ታጥቀው የቡራዩ ኬላ ላይ በፀጥታ አካላት ላይ ተኩስ በመክፈት የአርቲስት ሃጫለየ ሁንዴሳን አስከሬን መቀማታቸውን ለችሎቱ ገልጿል፡፡
ከተጠርጣሪዎቹ ጋር በተያያዘም የ10 ምስክሮች ቃል መቀበሉን እና ተጨማሪ ሌሎች የሰነድ ማስረጃዎችን መሰብሰቡን ገልፆ እነሱ በተኮሱት መሳሪያ 1 የፀጥታ አካል መሞቱን እና ሶስቱ መቁሰላቸውን በተተኮሰ ቀለሀ በምርመራ አረጋግጫለሁም ብሏል።
ተጠርጣሪዎቹ በጠበቆቻቸው በኩል መቃወሚያ ያቀረቡ ሲሆን የማረሚያ ቤት አያያዛቸው እንዲስተካከል ላቀረቡት ጥያቄም ፍርድ ቤቱ ፖሊስ ማስተካከያ እንዲያደርግ በማዘዝ ለተጨማሪ ምርመራ 12 ቀን ፈቅዷል።
በሌላ በኩል የባልደራስ አመራር አቶ እስክንድር ነጋ ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን በአዲስ አበባ በፈጠሩት ሁከት እና ብጥብጥ በአምስት ክፍለ ከተሞች ከ54 ሚሊየን ብር በላይ የሚሆን ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ገልፆ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጠይቆ ችሎቱም የ13 ቀን የምርመራ ጊዜ ፈቅዶለታል።
ሰኞ እለት ፍርድ ቤት ቀርበው የነበሩት አቶ በቀለ ገርባ እና ሌሎች 9 የጃዋር ጠባቂዎች ላይም በትናንትናው እለት ለፖሊስ ተጨማሪ 11 ቀን የምርመራ ጊዜ ተሰጥቶባቸዋል።
ውጤቱን ለመጠባበቅ ለሀምሌ 20 ቀን 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡
በታሪክ አዱኛ