ድርጅቱ ከሁለት ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር የአፈር ማዳበሪያ ለማጓጓዝ የሚያስችል ስምምነት ተፈራረመ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 6፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ቶን የአፈር ማዳበሪያ ለማጓጓዝ ከሁለት ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ስምምነት ተፈራረመ።
ድርጅቱ ስምምነቱን የተፈራረመው ዲ ኤች ኤል እና ከዳይመንድ ሺፕ ቡከር ከተባሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ሲሆን፥ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ቶን የአፈር ማዳበሪያ ከውጭ ሀገር ወደ አገር ውስጥ የሚጓጓዝ ይሆናል።
በስምምነቱ መሰረት ለ2012 ዓ.ም ምርት ዘመን 900 ሺህ ቶን ማዳበሪያ በዲ ኤች ኤል እንዲሁም 560 ሺህ ቶኑ በዳይመንድ ሺፕ ቡከር የሚጓጓዝ ይሆናል።
የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ስራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ መገርሳ እንደገለፁት፥ ማዳበሪያውን ለማጓጓዝ ድርጅቶቹ የተመረጡት በዘርፉ በቂ ልምድ ያላቸው መሆኑ በመረጋገጡ ነው።
ከዚህ በፊት በማጓጓዝ ሂደት ይታይ የነበረውን መዘግየት ለማስቀረት ታሳቢ በማድረግ ምርጫው መከናወኑን የተናገሩት አቶ ሮባ፥ አጠቃላይ የማጓጓዣ ወጭውም 42 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ይፈጃል ብለዋል።
የማጓጓዝ ሂደቱን የሚመራውና የሚያስተባብረው የትራንፖርት ሚኒስቴር መሆኑንም ገልጸዋል።
የመጀመሪያው ጭነት በዚህ ወር መጨረሻ ወደብ ላይ የሚደርስ ሲሆን፥ ከሰኔ 2012 ዓ.ም በፊት ሙሉ ለሙሉ ወደ ሀገር ውስጥ ገብቶ ይጠናቀቃልም ብለዋል።
ማዳበሪያው ቀጥታ በባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት አማካይነት እስከ ዩኒዬኖች የማድረስ ሂደቱ ይከናወናል።
ማዳበሪያው ከሞሮኮ፣ ቻይና፣ ግብፅ እና የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች የሚመጣ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።