Fana: At a Speed of Life!

የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የማህበረሰብ አቀፍ ንቅናቄና ምርመራ መጠናከር አለበት- ም/ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የተጠናከረ ማህበረሰብ አቀፍ ንቅናቄ እና ምርመራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለፁ።

የሚኒስትሮች ኮሚቴ በኮቪድ-19 ወረሽኝ ወቅታዊ ሁኔታና ቀጣይ አዝማሚያ፣ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም እንዲሁም ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ተወያይቷል።

በውይይቱ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅታዊ ሁኔታን የተመለከተ ጽሁፍ የጤና ሚኒስትር አማካሪ ዶክተር ስንታየሁ ፀጋዬ ቀርቧል።

ዶክተር ስንታየሁ የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ ከተከሰተበት ከመጋቢት ጀምሮ እስከ ሐምሌ ወር ያለውን የስርጭት ሁኔታ የተመለከተ መረጃ በጽሁፋቸው አቅርበዋል።

በዚህም በወረርሽኙ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከፆታ አንፃር 61 በመቶ ወንዶች፤ 39 በመቶ ሴቶች መሆናቸውንና በበሽታው ከተያዙት 92 በመቶ የሚሆኑት ሰዎች ምንም አይነት ምልክት እንደማያሳዩ አስረድተዋል።

የሞት ምጣኔው 1 ነጥብ 8 በመቶ መሆኑን ገልፀው 75 በመቶ የሚሆነው ሞት የተመዘገበው በአዲስ አበባ ከተማ መሆኑን ጠቁመዋል።

የ”መ” ህጎችን የሚባሉት መታጠብ፣ መራራቅና መሸፈን በተመለከተ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ማድረግ 75 በመቶ የጨመረ ቢሆንም መታጠብ እና መራራቅ ግን ባለበት ከ25 እስከ 30 በመቶ ላይ ነው ብለዋል።

የመመርመር አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱንና እስካሁንም ከ302 ሺህ በላይ ሰዎች መመርመር መቻሉን አስታውቀዋል።

የዛሬውን ሳይጨምር በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 8 ሺህ 475 መድረሱና ከእለት ወደ እለት ቁጥሩ እያደገ መምጣቱ አሳሳቢ መሆኑን ዶክተር ስንታየሁ አመላክተዋል።

ይህንን ወረሽኝ ለመከላከል እና ወረርሽኙን ተረድቶ የተሻለ እርምጃ ለመውሰድ የተጠናከረ ማህበረሰብ አቀፍ ንቅናቄ እና የምርመራ ዘመቻ ታሳቢ እየተደረገ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው፥ የመከላከል ሥራ ላይ በይበልጥ በመስራት የበሽታውን ስርጭት ለመግታት የተጠናከረ ማህበረሰብ አቀፍ ዘመቻ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፥ ከወረርሽኙ ስፋትና ስርጭት አንጻር እንዲሁም በህብረተሰቡ ዘንድ አሁን የሚታየው መዘናጋት የከፋ ችግር እንዳያስከትል በትኩረት መስራት እንደሚገባ አመላክተዋል።

ለዚህ ደግሞ ወረሽኙን በመግታት ስኬት ካገኙ አገራት ልምድ ከመውሰድ ባለፈ የእነርሱን መንገድ በመከተል ጠንካራ ሥራ መስራት እንደሚገባ አንስተዋል።

የመከላከል ዘመቻውን አገራዊ አጀንዳ በማድረግ እያንዳንዱ ዜጋ እንዲተገብር የተጠናከረ ማህበረሰብ አቀፍ ንቅናቄ እና ምርመራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስምረውበታል።

ለመከላከል ዘመቻው ቅድሚያ በመስጠትና ለዘመቻው ህዝቡን ከዳር እስከ ዳር በማስተባበር በማህበረሰብ አቀፍ ንቅናቄ ሁሉም ኃላፊነቱን እንዲወጣ ማድረግ ይገባል” ሲሉም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማስገንዘባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.