ህልማችን ልዕልና መር ነው – አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 1፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ህልማችን ልዕልና መር ነው ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ፡፡
አቶ አደም በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፥ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ወደ ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማሻገር ዓላማ አድርጎ የተነሳው የለውጥ ጉዟችን ሥድስት ዓመታትን ተሻግሯል ብለዋል፡፡
በዚህም ብልፅግና ፓርቲ ከተመሰረተ አምስት ዓመታትን አስቆጥሮ በታላላቅ ስኬቶች እና ድሎች ታጅበን ዛሬ ላይ ደርሰናል ሲሉም ገልጸዋል።
ፈተናዎችን ተሻግረን፣ ጋሬጣዎችን ገፈን፣ ሰንኮፎችን ነቃቅለን ሊሳኩ የማይችል የሚመስሉ ድሎችን ያሳካነው፣ ከባድ የሚመስሉ ወቅቶችን ለመሻገር አቅም ያገኘነው ህልማችን ልዕልና መር ስለሆነ ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡
በልዕልና መር ህልም እውን ማድረጊያ ጉዞ ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ድሎችን አሳክተን ሕዳሴ ግድብ ላይ ነፍስ ዘርተን፣ የሀገር ውስጥ የስንዴ ፍላጎትን ከማሟላት አልፈን ኤክስፖርት አድርገን፣ በአጠቃላይ በፈተናዎች ያልተረታ ዘርፈ ብዙ አማራጮች ያሉበት ኢኮኖሚ ገንብተን ኢትዮጵያን በማሻገር ላይ እንገኛለን ብለዋል።
የተወረወሩብንን ቀስቶች አምክነን፣ ለውድቀታችን የተመከሩ ዶሴዎችን በብልሀት ቀደን፣ የተሰነዘሩብንን ጥቃቶች ቀልብሰን በአይደፈሬ ኢትዮጵያዊ ማንነት ህልውናዋ የተጠናከረ ሀምራዊት ኢትዮጵያን በብልፅግናዊ ብሩሻችን እየሳልናት እንገኛለን ነው ያሉት።
ኮይሻን ገንብተን፣ ጎርጎራን አስውበን፣ ጨበራ ጩርጩራን መስርተን፣ የወንጪን ውበት ገልጠን፣ አዲስ አበባን እንደ ስሟ በአበባነት ተምሳሌት ቀርፀን ያልተቋረጠው የልዕልና መር የህልም ጉዞ ዛሬም የበሰቃ ሀይቅን ውበት ሊያጎላ ብቅ ብሏል ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ከአዋሽ ብሔራዊ ፓርክ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘው የ “ቤኑና መንደር” ግንባታ እነሆ ሌላኛው የልዕልና መር ጉዟችን ተጨማሪ ምስክርነት ሆኖ ዛሬ ለፍፃሜ መብቃቱ የተበሰረው በታላቅ ኩራት ነው ብለዋል፡፡
የ “ቤኑና መንደር” ግንባታ መጠናቀቅን አስመልክተውም የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።