Fana: At a Speed of Life!

ምርታማነትን ለማሳደግ በቅጅንት እየተሠራ ነው – አቶ ሙስጠፌ መሐመድ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 1፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የተያዘው ዕቅድ እንዲሳካ እየተሠራ ነው ሲሉ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ ገለጹ፡፡

ርዕሰ መሥተዳድሩ በፋፈን ዞን ሀሮሬስ ወረዳ የተጀመረውን የስንዴ ሰብል የመሰብሰብ ሥራ ጎብኝተዋል።

በዚሁ ወቅትም የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የተያዘው ዕቅድ ውጤታማ እንዲሆን እና በምግብ ሰብል እራስን ለመቻል ፓርቲው፣ መንግሥት እና ሕዝቡ በጋራ እየሠሩ ነው ብለዋል፡፡

የስንዴ ልማት መርሐ-ግብር እና ሌሎች የግብርና ልማት ሥራዎች የሕዝቡን በምግብ ሰብል እራስ መቻልን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ያለሙ ናቸው ማለታቸውን የክልሉ መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል፡፡

ክልሉ ለእርሻ ልማት የሚሆን ለም መሬት፣ ትላልቅ ወንዞችና ወጣት የሰው ኃይል ባለቤት መሆኑን ጠቅሰው ÷ ይህንን በመጠቀም በተለያዩ የግብርና ልማት ስራዎች ላይ የተጠናከረ ስራ መሠራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ይህም ከውጭ ዕርዳታ ጠባቂነት ከመላቀቅ ባሻገር የተለያዩ ምርቶችን ወደ ውጪ የመላክ አቅም ላይ ለመድረስ እንደሚቻል ያግዛል ነው ያሉት፡፡

በቀጣይ የዝናብ ወቅቶችን በመጠቀም የእርሻ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ መስራት እንደሚገባ አመላክተው÷ በግብርና ስራ የተሰማሩ አካላትን ለማበረታትና አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ መንግሥት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

ከሀሮሬስ ወረዳ ከደረሰው የስንዴ ሰብል 1 ሚሊየን 10 ሺህ ኩንታል ምርት እንዲሁም ከፋፈን ዞን 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል የስንዴ ምርት እንደሚሰበሰብ ይጠበቃል ተብሏል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.