Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል በመኸር ከተዘራው ሰብል ውስጥ ከ3 ሚሊየን ሄክታር በላይ ተሰብስቧል

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 6 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በሰብል ከተሸፈነው 4 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር መሬት ውስጥ እስካሁን 3 ነጥብ 1 ሚሊየን ሄክታሩ መሰብሰቡን የክልልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ሃላፊዎችና ሰራተኞች በዛሬው እለት በባህርዳር ዙሪያ ወረዳዎች የአቅመ ደካማና ሴት አርሶ አደሮችን ሰብል በዘመቻ ሰብስበዋል።

ዘመቻው እየጣለ ባለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ምክንያት በሰብሎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቅረፍና አርሶ አደሮች ሰብላቸውን በወቅቱ እንዲሰበስቡ ለማበረታታት ያለመ ነው ተብሏል።

በመኸር ወቅት በክልሉ በዘር ከተሸፈነው መሬት ውስጥ በ3 ሚሊየን 193 ሺህ 456 ሄክታር የሚገኘው ሰብል መሰብሰቡ ተገልጿል።

አብዛኛው ያልተሰበሰበው ሰብል ያልደረሰና በደጋማ የክልሉ አካባቢዎች የሚገኝ መሆኑም ተጠቅሷል።

አሁን ላይ በክልሉ ምዕራብ እና ምሥራቃዊ ክፍሎች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እየጣለ ሲሆን፥ ዝናቡ በዚህ ከቀጠለ በሰብል ላይ ጉዳት ስለሚያደርስ የደረሱ ሰብሎችን በፍጥነት መሰብሰብ ይገባል ተብሏል።

አስተያየታቸውን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የሰጡ አርሶ አደሮችም ሰብልን በዘመቻ የመሰብሰቡ ሂደት የምርት ብክነትን እንደሚያስቀር ተናግረዋል።

በዙፋን ካሳሁን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.