የቀጣይ አቅጣጫችን ሁሉን ባሳተፈ መልኩ ሥራን በትግል መምራት ነው- አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ተጠያቂነትን ባረጋገጠና ሁሉን ባሳተፈ መልኩ ሥራን በትግል መምራት የብልጽግና ፓርቲ የቀጣይ አቅጣጫ መሆኑን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ፡፡
የብልፅግና ፓርቲ የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ መድረክ ተጠናቅቋል።
በመድረኩ ላይ አቶ አደም ፋራህን ጨምሮ የዋናው ጽሕፈት ቤት፣ የክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የፓርቲው ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ባለፉት ሶስት ወራት እንደ ፓርቲ የተከናወኑ ተግባራት አፈጻጸም የተገመገመ ሲሆን÷ ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫም ተቀምጧል።
የፓርቲው የሩብ ዓመት ግምገማ በተሳካ ሁኔታ መከናወኑንም አቶ አደም ተናግረዋል።
በየጊዜው ራሱን በአግባቡ እያስተማረና እያደገ የሚሄድ ፓርቲ መሆን፣ የመንግስት እቅዶችን በብቃት መፈጸምና የክትትልና ድጋፍ ስርዓትን ማጠናከር የፓርቲው ዋና ጽሕፈት ቤትና የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ተልዕኮዎች መሆናቸውንም አስገንዝበዋል፡፡
ይህን መሰረት በማድረግም በሩብ ዓመቱ በፓርቲው የተከናወኑ ስራዎች ላይ ጥልቅ ግምገማ ተደርጓል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በዚህም በሩብ ዓመቱ እንደ ገዥ ፓርቲ ቃልን በተግባር ለመፈጸም የሚያስችሉ ውጤታማ የንቅናቄ ስራዎች በማከናወን በእቅድ የተያዙ ስራዎችን ማሳካት ተችሏል ነው ያሉት።
ለአብነትም በግብርና በጤና እና ሌሎች ማህበራዊ ዘርፎች እንዲሁም በፖለቲካና ጸጥታ ስራዎች ለውጥ ተመዝግቧል ብለዋል።
ሁለንተናዊ ብልጽግናን የሚያረጋግጡ ተግባራትን በፍጥነት ከማከናወን አኳያም እመርታ ታይቷል ነው ያሉት፡፡
ፓርቲው በአጭር ጊዜ ለ14 ሚሊየን አባላትና አመራሮቹ ስልጠና መስጠት መቻሉን ጠቅሰው÷ የአሰራር ስርዓቶችንም በፍጥነት በማጠናቀቅ ተግባራዊ ማድረግ መቻሉን አብራርተዋል፡፡
በሁሉም የፓርቲው መዋቅሮች መካከል የተቀራረበ የአፈጻጸም አቅም እየተገነባ መምጣቱንም ነው የተናገሩት።
ባካሔድናቸው ውይይቶች ልምዶችና ተሞክሮዎችን ከመቅሰም ባሻገር በቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ የተሻለ መግባባት ፈጥረናል ሲሉም አስረድተዋል፡፡
በቀጣይም ሁሉንም ስራዎች በጥራት መስራት እንዲሁም የተጀመሩ የሪፎርም ስራዎችን ተቋማዊና ስርዓታዊ ማድረግ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
አመራሩ የህዝብን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማረጋገጥ እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ወርዶ መስራትና መደገፍ ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ አመላክተዋል፡፡
ብልጽግና ፓርቲ ቃልን በተግባር በመፈጸም የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የጀመራቸውን ሥራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡
ተጠያቂነትን ባረጋገጠና ሁሉን ባሳተፈ መልኩ ሥራን በትግል መምራት የቀጣይ አቅጣጫ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡