ኢትዮጵያ ከጃፓን መንግሥት ጋር የ11 ሚሊየን ዶላር የድጋፍ ስምምነት ተፈራረመች
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በሲዳማ ክልል የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ለማሻሻል ለሚተገበረው ፕሮጀክት የሚውል የ11 ሚሊየን ዶላር የድጋፍ ስምምነት ከጃፓን መንግሥት ጋር ተፈራረመች፡፡
ስምምነቱን የተፈራረሙት የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ፣ በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪ እና በኢትዮጵያ የጃፓን ዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) ዋና ተወካይ ኦሺማ ኬንሱኬ ናቸው፡፡
ፕሮጀክቱ በሲዳማ ክልል የሚገኙ 3 ሺህ 600 ተማሪዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ መገለጹን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡
በዚህም ለመማር ማስተማሩ አጋዥ የሆኑ ቁሳቁሶች የተካተቱላቸው አምሥት አዳዲስ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንደሚገነቡ ተገልጿል፡፡
አቶ አሕመድ በስምምነት ፊርማው ላይ÷ የጃፓን መንግሥት በድህንት ቅነሳ፣ ሰላም እና መረጋጋት ዘርፎች ለሚያደርገው ያልተቋረጠ ድጋፍ ምሥጋና አቅርበዋል፡፡
ኢትዮጵያ ዘላቂ ኢኮኖሚን ለመገንባት እያደረገች ያለችውን የሪፎርም ሥራዎች አብራርተው÷ እንደ ጃፓን ዓይነት አጋር ሀገራት የማይቋረጥ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡
አምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪ በበኩላቸው÷ በድጋፉ የሚገነቡት ትምህርት ቤቶች በሲዳማ ክልል የሚገኙ ተማሪዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡
ድጋፉ በኢትዮጵያ እና ጃፓን መካከል ያለውን ዘርፈ-ብዙ ግንኙነት በይበልጥ እንደሚያጠናክረውም ገልጸዋል፡፡