Fana: At a Speed of Life!

የአየር መንገዱ ሠራተኞች ለኢትዮጵያ ቱሪዝም አምባሳደር ሆነው ይሰራሉ-የኢትዮጵያ አየር መንገድ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2012  (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአገሪቷን የቱሪዝም እድገት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ የተለያዩ ፓኬጆችን ቀርጾ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

በኢትዮጵያ እምብዛም ያልተሰራበትን የቱሪዝም ዘርፍ ለማሳደግና ከዚህም የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ መንግስት መስኩን ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ በማድረግ በመዲናዋ ትላልቅ ፓርኮችን እየገነባ ነው።

አየር መንገዱም የዘርፉን ዕድገት ማሳደግን እንደ ዋነኛ ስራው ይዞ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታውቋል።

የአየር መንገዱ የዓለም አቀፍ አገልግሎት ዋና ኃላፊ አቶ ለማ ያዴቻ ÷አየር መንገዱ ከሚያጓጉዛቸው መንገደኞች 70 በመቶ ያህሉ ኢትዮጵያን መሸጋገሪያ በማድረግ ወደ ሌላ አገር ይጓዛሉ።

ከእነዚህ መካከል 50 በመቶዎቹን በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ አዲስ አበባን እንዲጎበኙ ለማድረግ በትኩረት እየሰራን ነው ብለዋል።

በተለያዩ አገራት የሚገኙ የአየር መንገዱ ስራ አስኪያጆችም ይህን ትልቅ ተልዕኮ በመውሰድ ጎብኚዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ እየሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል።

ሁሉም የአየር መንገዱ ሠራተኞች ለኢትዮጵያ ቱሪዝም እንደ አምባሳደር በመሆን እያገለገሉ እንደሆነም ነው የተናገሩት ።

የተለያዩ ፓኬጆች መዘጋጀታቸውን ገልጸው÷ ጎብኚዎች በሠዓታት ቆይታቸው አዲስ አበባን መጎብኘት የሚያስችላቸውን ‘አዲስ ናይት ላይፍ’ የተሰኘ ፓኬጅ ለአብነት አንስተዋል።

”አየር መንገዱ የኢትዮጵያን ቱሪዝም ዘርፍ ይቀይራል” ያሉት አቶ ለማ በ127 መዳረሻዎች የሚገኙ የስራ ኃላፊዎችም በዚህ ላይ እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የአየር መንገዱ ጥረት እንደ አገር ቱሪዝሙን ለማሳለጥ የሚጎለውን ነገር በመካከል ሆኖ ለመሙላት መሆኑን ሀላፊው መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.