Fana: At a Speed of Life!

ብልጽግና ፓርቲ ባለፉት 5 ዓመታት ኢትዮጵያን ከስብራት ወደ ልዕልና የሚያሸጋግሩ ድሎችን አስመዝግቧል – ም/ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 21፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ብልጽግና ፓርቲ ባለፉት አምስት ዓመታት ኢትዮጵያን ከስብራት ወደ ልዕልና የሚያሸጋግሩ ድሎችን አስመዝግቧል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ፡፡

የብልጽግና ፓርቲ 5ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የማጠቃለያ መርሐ ግብር በዓድዋ ድል መታሰቢያ ተካሂዷል።

ም/ጠ/ሚ ተመስገን በዓሉን አስመልክተው በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ ዛሬ “የሃሳብ ልዕልና ለሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ሃሳብ በተካሄደው የፓርቲያችን ብልጽግና 5ኛ ዓመት ምሥረታ በዓል የማጠቃለያ መርሐ ግብር ላይ ተገኝተናል ብለዋል።

“በድርጅት ሳቢነትና በሕዝብ ገፊነት በመጣው ለውጥ የተወለደው ፓርቲያችን ብልጽግና፣ ባለፉት አምስት ዓመታት ኢትዮጵያን ከስብራት ወደ ልዕልና የሚያሸጋግሩ ድሎችን አስመዝግቧል” ብለዋል።

በጉዟችን አያሌ ፈተናዎችን ቀልብሰናል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የልዩነት ግንብን አፍርሰናል፤ ፓርቲያችንም የተግባር ምሳሌ መሆኑን በአካታች የፖለቲካ መሥመሩ አሳይቷል ነው ያሉት።

በዚህም ሀገርን ከመስቀለኛ ወደ ትክክለኛ የከፍታ ጎዳና አምጥቷል ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና በማኅበራዊ ዘርፎች የትውልድ ዐሻራ የሆኑ እመርታዎች መጥተዋል፤ በሳልና ደፋር የዲፕሎማሲ አካሄድን በመከተል ብሔራዊ ጥቅማችንን ያስከበሩ ድሎችን ተቀዳጅተናልም ብለዋል።

ሰላም ወዳዱ ሕዝባችን የመንገዳችንን አዋጪነት እየተረዳ ለሁለንተናዊ ሰላምና ዕድገት እያደረገ ላለው ተሳትፎ በፓርቲያችን ስም ማመስገን እፈልጋለሁ ሲሉም በፅሑፋቸው ገልፀዋል።

ፓርቲው ኢትዮጵያ በዓለም የፖለቲካና የኢኮኖሚ መድረክ የሚገባትን የመሪነት ሚና እንድትጫወት የሚያስችሉ ልዕልና መር ሕልሞችን ለማሳካት ያለ ዕረፍት እንደሚሠራም አረጋግጠዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.