Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና ፓኪስታን በንግድ ዘርፍ ያላቸውን ትብብር እንደሚያጠናክሩ ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 21፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና ፓኪስታን በንግድ ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ለማስፋት እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡

በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር ከፓኪስታን የንግድ ሚኒስትር ጃም ከማል ካን ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም ሁለቱ ሀገራት በንግዱ ዘርፍ በተለይም በሀገራቱ የንግድ ማህበረሰብ መካከል ያለውን የንግድ ትስስር ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል፡፡

አምባሳደር ጀማል÷ስለ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ የግብርና ምርታማነት ስራዎች፣ የንግድ ስራ ምቹነትን ለማሻሻልና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን አስመልክተው ገለጻ አድርገዋል።

ለረጅም ጊዜ የቆየ ወዳጅነት ያላቸው ኢትዮጵያና ፓኪስታን ንግድ፣ ባህል፣ አቪዬሽን፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ያላቸው የሁለትዮሽ ትብብር እያደገ መምጣቱን አንስተዋል።

ጃም ከማል ካን በበኩላቸው÷ሚኒስቴሩ እና የፓኪስታን የንግድ ልማት ባለስልጣን በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን እንዲካሄድ አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረጉ እንደሚገኙ መግለጻቸውን የኤምባሲው መረጃ ያመለክታል፡፡

ፓኪስታን በፖሊሲ ማዕቀፏ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላትን ትስስር ለማጠናከር እንደምትሰራ እና ሁለቱ ሀገራት በንግዱ ዘርፍ ያላቸውን ግንኙነት ለማስፋት እንደሚሰሩም ገልጸዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.