የብልጽግና ፓርቲ 5ኛ ዓመት የምስረታ በዓል አባላትና ደጋፊዎች በተገኙበት በጅቡቲ ተከበረ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 22፣ 2017(ኤፍ ቢ ሲ) የብልጽግና ፓርቲ አምስተኛ ዓመት የምስረታ በዓል “የሐሳብ ልዕልና ለሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ሐሳብ በጅቡቲ የሚኖሩ አባላትና ደጋፊዎች በተገኙበት ተከብሯል።
በመርሐ-ግብሩ ላይ በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የፓርቲው የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምክትል ዘርፍ ኃላፊ ተስፋሁን ጎበዛይ እንዳሉት÷ ብልጽግና ባለፉት አምስት ዓመታት በብዙ ተግዳሮቶች መካከል በጽናት በመሥራት ተከታታይ ድሎችን አስመዝግቧል፡፡
“የህልም ጉልበት ለዕምርታዊ ዕድገት” በሚል የመወያያ ሠነድ በመድረኩ የቀረበ ሲሆን፥ በወቅቱም ያጋጠሙት ተግዳሮቶች፣ ያስመዘገባቸው ድሎች፣ አሁን ያሉ ተስፋዎችን ጨምሮ የወደፊት ራዕዩች ላይ ውይይት ተደርጓል።
ባለፉት አምስት ዓመታትም በግብርና፣ አረንጓዴ ዐሻራ፣ ሌማት ትሩፋት፣ ፕሮጀክት ግንባታ፣ የተቋማት ሪፎርም፣ በቱሪዝም ማስፋፊያ፣ በኢንዱስትሪ ግንባታ እና ሌሎች በርካታ የልማት ሥራዎች መከናወናቸው ተብራርቷል፡፡
የሰላም ጥሪ መሠረታዊ የፓርቲው አቋም መሆኑን ገልጸው፥ ሕዝባዊ መድረኮችና ውይይቶች በየደረጃው በማዘጋጀት ብሔራዊ መግግባትን በማምጣት ረገድ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የወል ትርክቶችን ገዢ በማድረግና ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር አብሮ በመሥራት የአንድነት ተምሳሌት በመሆን የተጀመሩ ተግባራት ይበል የሚያሰኙ ናቸው ማለታቸውን የፓርቲው መረጃ አመላክቷል፡፡