Fana: At a Speed of Life!

የሳርቤት አደባባይ-መካኒሳ-ፉሪ ሀና የኮሪደር ልማት የስራ ሂደት ተገመገመ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 22፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ከሳርቤት አደባባይ-መካኒሳ-ፉሪ ሀና በመገንባት ላይ የሚገኘውን የኮሪደር ልማት የስራ ሂደት መገምገሙን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው እንዳመለከቱት፤ የኮሪደር ልማት ስራው 18 ኪ.ሎ ሜትር የሚሸፍነው ነው።

በአካባቢው ያለውን ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ለማቃለል የመንገድ ደረጃውን ማሻሻል፣ የአረንጓዴ ልማት፣ የህዝብ መዝናኛ ፕላዛዎች፣ የህጻናት መጫዎቻዎችና ሰፊ የእግረኛ መንገድ ማካተቱን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የተሽከርካሪ ማቆሚያዎች፣ የታክሲና አውቶቡስ መጫኛና ማውረጃ ተርሚናሎች እንዲሁም ለረዥም ጊዜ ግንባታቸዉ ሳይጠናቀቅ የቆዩ ህንጻዎችን በፍጥነት በማጠናቀቅ ወደ አገልግሎት የማስገባት እና ነባር ህንፃዎችን የማደስ ስራዎችን ማካተቱን ጠቁመዋል።

በከተማ ደረጃ ከጀመርነው የኮሪደር ልማት ስራ በተጨማሪ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማም ማህበረሰቡን በማስተባበር ተጨማሪ የአረንጓዴ ልማት ስራዎችን በመገንባት ላይ ይገኛል ብለዋል።

የኮሪደር ልማት ስራው በአቃቂ ቃሊቲ ከተጀመረው ጋር የሚገጥም ይሆናል ሲሉ ጠቁመዋል።

በዛሬው ጉብኝታችን አንዳንድ ቅሬታ የቀረበባቸዉ ጉዳዮችን በቦታዉ በመገኘት ከባለ ጉዳዮቹ ጋር ተመካክረን ፈትተናል ያሉት ከንቲባዋ፤ ስራው በፍጥነት እና በጥራት እንዲከናወን ከከተማ አስተዳደሩ ጎን በመቆም እየደገፉ ያሉ ነዋሪዎች አመስግነዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.