የሰላም ስምምነቱ በኦሮሞ ሕዝብ የፖለቲካ ትግል ታሪክ ውስጥ ታላቁ ምዕራፍ ነው – አቶ ሽመልስ አብዲሳ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 22፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት እና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት በኦሮሞ ሕዝብ የፖለቲካ ትግል ታሪክ ውስጥ ታላቁ ምዕራፍ ነው ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ።
አቶ ሽመልስ በዛሬው ዕለት የተፈረመውን የሰላም ስምምነት በማስመልከት በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ የለውጡ መንግሥት የሰላም እጦት እና ለሕዝብ ስቃይ ምንጭ የሆነውን የፖለቲካ ልዩነት በሰላማዊ ውይይት ለመፍታት በቁርጠኝነት ሲንቀሳቀስ እንደነበር አስታውሰዋል።
የኦሮሞ ልሂቃን፣ አባገዳዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ሀደ ሲንቄዎች እና የኦሮሚያ ሰላም ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች ሁሉ ልዩነቶች በሰላማዊ መንገድ መፍትሄ እንዲያገኙ ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርጉ እንደነበር አስታውሰዋል።
በተለይም ሰፊው የኦሮሞ ሕዝብ ልዩነቶች ሰላማዊ መፍትሔ እንዲያገኙ ያልተቋረጠ ጥረት በማድረግ የሰላም ጥሪ ሲያቀርብ እንደነበር ጠቅሰዋል።
በዚህም መሰረት የኦሮሚያ ክልል መንግስት ለሰላማዊ ውይይት ያለውን ቁርጠኝነት በመገንዘብና ለዚህም ዕውቅና በመስጠት የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት የቀረበውን የሰላም ጥሪ ሊቀበል መቻሉን ገልጸዋል።
በዚህም መሰረት በዛሬው ዕለት የተከናወነው ታሪካዊ የሰላም ስምምነት እውን ሊሆን መቻሉን አመልክተዋል።