የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ኮምቦልቻ ቅርንጫፍ መጋዝን ተመረቀ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 22፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በ85 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ኮምቦልቻ ቅርንጫፍ መጋዝን እና ሌሎች የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ተመርቀዋል፡፡
በዚህ ወቅት የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)÷ የውጭ ንግድ ግብይትን በማሳለጥና ጥራትን በማሳደግ እንዲሁም የምርት ገበያ ተቋማትን በማጠናከር 6 ቢሊየን ዶላር ለማግኘት መታቀዱን ገልፀዋል።
ከጥራጥሬና የቅባት እህሎች ከ750 ሚሊየን ዶላር በላይ ለማግኘት መታቀዱን ጠቅሰው÷ የተመረቁት መጋዝኖች የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ኮምቦልቻ ቅርንጫፍ አገልገሎቱን ለማሳለጥ እና የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት ያግዛሉ ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አብዱ ሁሴን÷ በአማራ ክልል በ2016/17 የምርት ዘመን 10 ነጥብ 9 ሚሊየን ኩንታል የወጪ ንግድ ምርት በማምረት 1 ቢሊየን ዶላር ለማግኘት መታቀዱን ጠቅሰዋል፡፡
እቅዱን ለማሳካትም በክልሉ ባሉ ስምንት ሪጆፖሊታንት ከተሞች 1ኛ ደረጃ የግብይት ማዕከላትን ለመገንባት ከ450 ሚሊየን ብር በላይ በጀት መመደቡን ገልፀዋል፡፡
የነዚህ ማዕከላት ግንባታ ሲጠናቀቅ የተራዘመ የግብይት ሰንሰለትን በማስቀረት ኑሮ ውድነትን ይቀንሳል ብለዋል።
በከድር መሀመድ