መቄዶንያ የሰው ልጆች ያለምንም ልዩነት የሚደገፉበት ማዕከል መሆኑ ተነገረ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 22፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) መቄዶንያ የአረጋውያንና የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል የሰው ልጆች ያለምንም የሀይማኖት፣ የዘር፣ የቀለም ልዩነት የሚደገፉበት ማዕከል መሆኑ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከማዕከሉ ጋር በመተባበር የፀሎት መርሐ ግብር የሃይማኖት ተቋማት መሪዎችና አባቶች በተገኙበት አካሂዷል።
‘ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው” በሚል መርህ የተመሰረተው ማዕከሉ፤ በእርጅና ዘመን ጧሪ ያጡትን፣ በከፍተኛ ህመም የሚሰቃዩና ረዳት የሌላቸው ወገኖችንና የአዕምሮ ህሙማንን መንከባከብ ዓላማ አድርጎ የተቋቋመ ነው።
በመርሐ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ ሰላም ለሰው ልጅ ሁሉ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፥ ሁሉም ከጥላቻ፣ ከቂም፣ከጦርነትና ከበቀል መራቅ አለበት ብለዋል።
ተስፋ፣ ዕድገትና ብልፅግናን ለማረጋገጥ በቀዳሚነት ሰላም ያስፈልጋል በማለት አክለዋል።
በኢትዮጵያ ሰላም ሰፍኖ የሚጠበቀው አንድነትና ዕድገት እንዲመጣ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ዘርና ሀይማኖት ሳይገድበን በአንድነት ለሰላም መቆም አለብን ብለዋል።
የመቄዶንያ በጎ አድራጎት ማህበር መስራች ቢንያም በለጠ በበኩላቸው፥ ማዕከሉ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች በሚገኙ 44 ቅርንጫፎቹ ከ8 ሺህ በላይ አረጋዊያንና የአዕምሮ ህሙማንን እየረዳ እንደሆነ ገልጸዋል።
በቀጣይም ቅርንጫፎቹን ወደ 240 ለማድረስ እየሰራ እንደሚገኝ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
መቄዶንያ ማለት ትንሿ ኢትዮጵያነች ያሉት አቶ ቢኒያም፥ የሀይማኖት፣ የዘር፣ የቀለም ልዩነት ሳይኖር ሁሉም የሚደገፉበት ነው ብለዋል።
ማዕከሉ የምግብና መጠለያ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰው፥ የሃይማኖት ተቋማትም መንፈሳዊ ትምህርት እየሰጡ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሀይማኖት ተቋማት ፕሮግራሙን በማዘጋጀትና የማዕከሉን የስራ እንቅስቃሴ በመጎብኘቱ አመስግነዋል።
መቄዶንያን መርዳት የሚፈልጉ በአጭር የጽሑፍ መልዕክት እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አካውንት በሆነው 8161 አማካኝነት ድጋፍ እንዲያደርጉ መልዕክት አስተላልፈዋል።