ቴክ

በኢትዮጵያዊው ወጣት የተሰሩ ሁለት የድሮን ፈጠራ ውጤቶች ይፋ ሆኑ

By Tibebu Kebede

July 20, 2020

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያዊው ወጣት ናኦል ዳባ የተሰሩ ሁለት ድሮንና አንድ የኮሮና ቫይረስ ሙቀት መለኪያ የፈጠራ ውጤቶች ይፋ ሆኑ።

በወጣት ናኦል ዳባ የተሰሩት ለግብርና እና ለተግባቦት ዘርፍ አገልግሎት የሚውሉ ሁለት የድሮንና ከእጅ ንክኪ ነጻ የሆነ የኮሮና ቫይረስ ሙቀት መለኪያ የፈጠራ ውጤቶች ናቸው።

የድሮን ፈጠራ ውጤቶቹ ፀረ አረም መድሃኒት መርጫና ከርቀት ሆኖ ለማኅበረሰቡ መልክዕት ማድረስ የሚያስችሉ ናቸው ተብሏል።

የፈጠራ ውጤቶቹ ባለቤት ወጣት ናኦል ዳባ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የዕድገት ጉዞ በቴክኖሎጂ ለመደገፍ የፈጠራ ስራውን ማበርከቱን ገልጿል።

ዓለም አቀፍ ስጋት የሆነውን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከላከል ደግሞ በስራዎቹ ቅድሚያ እንደሰጣቸው ነው የተናገረው።

ለግብርና ዘርፍ የሚያገለግለው ፀረ አረም መርጫ ድሮንም 10 ሊትር የመያዝ አቅም ያለውና በአንድ ጊዜ 65 ሄክታር መሬት መርጨት የሚችል ሲሆን ይህም የሰው ሃይል ጉልበትን ይቀንሳል።

ሁለተኛው ከርቀት ሆኖ መልክዕት ለማኅበረሰቡ ማድረስ የሚያስችለው ድሮንም የኮሮና ግንዛቤ መፍጠሪያ መልዕክቶችን ለማስተላለፍ እንደሚያግዝ ገልጿል።

ሶስተኛ የፈጠራ ውጤት የሆነው ከሰው ንክኪ ነጻ በሆነ መንገድ ሙቀት መለካት የሚያስችለው ቴክኖሎጂ እጅን በማስጠጋት ከንክኪ ነጻ በሆነ መንገድ እንዲሰራ ተደርጎ የበለጸገ ሲሆን ማንኛውም ሰው ማሽኑ ባለበት ቦታ ሳይለካ ካለፈ ድምጽ ያሰማል።

የሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኮሎኔል ወሰንየለህ ሁነኛው እስካሁን በድሮን ዘርፍ ፈቃድ የሚሰጥበት አሰራር እንዳልነበረ አውስተዋል።

አሁን አሰራሩን የሚፈቅድ ህግ በመርቀቁ የፈጠራ ባለቤቱ ወጣት ናኦልና ሌሎች መስፈርቱን አሟልተው ሲገኙ ፈቃድ እንደሚሰጥ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።