Fana: At a Speed of Life!

የመዲናዋ ሆቴሎች ለአፍሪካ መሪዎች ጉባዔ እንግዶችን ለማስተናገድ ዝግጅት እያደረጉ ነው

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 24፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ሆቴሎች ለአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ የሚመጡ እንግዶችን ለማስተናገድ አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን የአዲስ አበባ ሆቴል ባለቤቶች ማህበር አስታውቋል፡፡

የማህበሩ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ አስቴር ሰለሞን እንደገለጹት÷ሆቴሎች የጉባዔው ተሳታፊዎችን የሚመጥን መስተንግዶ ማድረግ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ውይይት ተደርጓል።

በዚህ መሰረትም ሆቴሎች ኢትዮጵያዊ ጨዋነት የተላበሰና ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት ለመስጠት አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ ጀምረዋል ብለዋል።

ሆቴሎች ደረጃውን የጠበቀና በቴክኖሎጂ የታገዘ ሁሉን አቀፍ አገልግሎት ለመስጠት እየሰሩ መሆኑን ነው ያስረዱት።

የሚሰጡ አገልግሎቶች የኢትዮጵያን ባህል እና እሴት የሚያንጸባርቁ እንዲሆኑ በትኩረት እየተዘጋጁ እንደሆነም ጠቁመዋል።

የቡና አፈላል ሥርዓት፣ ባህላዊ ምግቦች፣ ባህላዊ ጭፈራዎችና ሌሎች ኩነቶችን ለእንግዶች ለማስተዋወቅ እየሰሩ መሆኑን ወ/ሮ አስቴር ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡

እንግዶች በቆይታቸው ደህንነታቸው ተጠበቆ አይረሴና ስኬታማ ጊዜ እንዲያሳልፉም ከመዲናዋና ከፌደራል ጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ጠቅሰዋል።

የውሃ፣ መብራት፣ ስልክ እና ሌሎች አገልግሎቶች መቆራረጥ እንዳያጋጥም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር ይሰራል ብለዋል።

ሕብረተሰቡም ለጉባዔው የሚመጡ እንግዶችን በተለመደው የኢትዮጵያ እንግዳ አቀባበል ሥርዓት አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.