10 ኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ተሸጋገሩ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 24፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የሚያስተዳድራቸው 10 ኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ማደጋቸውን ኮርፖሬሽኑ አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው 13 ኢንዱስትሪ ፓርኮች እና የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ላይ ግምገማ አድርጓል።
በዚህም አዳማ፣ ባህርዳር፣ ቦሌ ለሚ፣ ደብረ ብረሃን፣ ሀዋሳ፣ ጅማ፣ ቂሊንጦ፣ ኮምቦልቻ፣ መቀሌ እና ሰመራ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ዞንነት እንዲያድጉ መወሰኑን የኮርፖሬሽኑ መረጃ አመላክቷል፡፡
ፓርኮቹ ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ዞንነት ማደጋቸው የግል ዘርፉ በኢኮኖሚ፣ በንግድ፣ በአገልግሎት እና ሌሎች ልማታዊ ኢንቨስትመንቶች ላይ እንዲሳተፉ ለማበረታታት፣ የኢኮኖሚ ክላስተሮችን ለማስተዋወቅ፣ የስራ ዕድሎችን ለመፍጠርና ሌሎች ዘርፈብዙ ፋይዳዎች እንደሚኖሩት ተጠቁሟል፡፡
በተጨማሪም ንግድን፣ ዕቃን ወደ ውጭ የመላክ አፈፃፀም እና ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ዕቃዎችን በሀገር ውስጥ ምርቶች የመተካት አቅም ለማሳደግ፣ በዓለም ዓቀፍ የንግድ ሰንሰለት የሚኖር ቁርኝትን ለማስፋፋት እና ዘላቂ ዕድገት ለማምጣት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖራቸው ይታመናል፡፡