Fana: At a Speed of Life!

የአቢጃታ ሐይቅ ህልውና …

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 24፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ከአጠቃቀም ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የህልውና ስጋት ላይ ወድቆ የነበረው የአቢጃታ ሐይቅ ወደቀደመው ይዞታው እየተመለሰ መሆኑን የአብጃታ ፓርክ ዋና ሃላፊ አቶ አስቻለው ጸጋዬ ገለጹ፡፡

የአቢጃታ ፓርክ ዋና ሃላፊ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳሉት፥ በኦሮሚያ ክልል የሚገኘው የአቢጃታ ሻላ ብሔራዊ ፓርክ 482 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑ እንደ አቢጃታ፣ ሻላ እና ጭቱ ሐይቆች አሉት፡፡

ሆኖም እስከ 2011 ዓ.ም ድረስ በተለያዩ ምክንያቶች አቢጃታ ሐይቅ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በዚህም 194 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የነበረው የሃይቁ ስፋት ወደ 66 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ዝቅ በማለት ሃይቁ የመጥፋት ስጋት ተጋርጦበት ነበር፡፡

ከ2011 ዓ.ም በኋላ ግን የሐይቁን ስጋት ለመቅረፍ ከባለድርሻ አካላት ጋር ንቅናቄ በማዘጋጀት የተለያዩ ስራዎች መጀመራቸውን ያነሳሉ፡፡

በዚህም ፕሮጀክቶችን በመንደፍ እንደ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በመስራትና ወጣቶችን በማደረጀት እንዲሁም ለህብረተሰቡ ግንዛቤን በመፍጠር ፓርኩ ወደቀደመው ይዞታው እንዲመለስና እንዲጠበቅ ተደርጓልም ብለዋል፡፡

አሁን ላይም በፓርኩ ውስጥ የሚገኘው የአቢጃታ ሐይቅ ወደቀደመው 194 ስኩዬር ኪሎ ሜትር እየተመለሰ እንደሚገኝም ነው የገለጹት፡፡

በዚህም ሥራ የዓሣ ሃብት ተመልሷል፤ የዓሣ መመለስ ዓሣ ተመጋቢ አዕዋፋት በአካባቢው ይገኛሉ፤ የሜዳ ፍየሎችንና የቆላ አጋዘንን ጨምሮ ሌሎች የዱር እንስሳት በሐይቁ አቅራቢያ በድጋሚ እየታዩ ነውም ብለዋል አቶ አስቻለው፡፡

በዚህ የህበረተሰብ ንቅናቄ ዘላቂ የሆነ የህብረተሰብ ተጠቃሚነት በማስፋት የኔነት ስሜት በማሳደር የተለያየ የስራ ዕድል በመፍጠር ፓርኩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራበት መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም የተለያዩ አጋር ድርጅቶች ፓርኩ እንዲጠበቅ ጉልህ አስተዋጽዖ ማበርከታቸውም ነው የተነሳው፡፡

በመሰረት አወቀ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.