Fana: At a Speed of Life!

የምርት ነጻ ዝውውርን የሚገድቡ 283 ህገ ወጥ ኬላዎች በመላ ሀገሪቱ እንደሚገኙ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለፁ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 24፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የምርት ነጻ ዝውውርን የሚገድቡና የሎጂስቲክስ ቅልጥፍናን የሚገድቡ 283 ህገ ወጥ ኬላዎች በመላ ሀገሪቱ በሁሉም ክልሎች ተንሰራፍተው ይገኛሉ ሲሉ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 8ኛ መደበኛ ስብሰባውን ያካሄደ ሲሆን÷የምክር ቤት አባላት ለሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) የተለያዩ ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡

ሚኒስትሩ የምክር ቤቱ አባላት ላቀረቡት ጥያቄ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ ÷ የቀረጥና ታክስ ጉዳይ ትኩረት የሚያስፈልገው ጉዳይ መሆኑን ገልፀው ኬላ ይነሳ ተብሎ በመንግስት ደረጃ ቢወሰንም የተለያዩ ሰበቦች እየተፈለጉ 283 ህገ ወጥ ኬላዎች በመላ ሀገሪቱ ተንሰራፍተው ይገኛሉ ብለዋል፡፡

ህገ ወጥ ኬላዎች የምርት ነጻ ዝውውርን የሚገድቡና የሎጂስቲክስን ቅልጥፍናን የሚገድቡ፣ በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ጫና ያላቸው ጉዳዮች መሆናቸውን በማወቅ ምክር ቤቱን የራሱን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያ ከተጀመረ ጀምሮ እስካሁን ድረስ በየቀኑ የገበያ ክትትልና ቁጥጥር ስራዎች ተከናውነዋል ያሉት ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)÷ ባለፉት 5 ወራት ከ105 ሺህ በላይ የኑሮ ውድነቱ እንዲባባስ ያደረጉ ነጋዴዎች ላይ ርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል፡፡

ባለፉት ወራት መሰረታዊ ሸቀጦች ሲቀርቡ የነበሩት በመንግስት ሳይሆን በግሉ ሴክተር እንደነበር አስታውሰው÷በተለይ በፍራንኮ ቫሉታ አማካኝነት 208 ሚሊየን ሊትር ዘይት ከውጭ ወደ ሀገር ገብቶ ገበያውን እንዳረጋጋ አንስተዋል፡፡

ህብረተሰቡ በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የግብይት ማዕከላት ላይ ምርት እንዲገዛ በማሳሰብ በቂ ሼድ ያለውና የምርት ጥራት የሚጠበቅበት የግብይት ማዕከላትም በሁሉም ክልሎች እየተገነቡ ነው ብለዋል፡፡

ከሚታሰበው ልክ አንፃር ገና ቢንሆንም አሁን ላይ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት አንጻር ሲታይ ግን በጥራት መሰረተ ልማት ግንባታ እንዲሁም በብዛትና በጥራት ማምረት ላይ ኢትዮጵያ ቀዳሚውን ስፍራ ይዛለች ብለዋል፡፡

በብዛት የማምረትን ሥራ አጠናክሮ ማስቀጠል፣ ለጥራት ተገቢውን ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል በሚል ከ8 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ የጥራት መንደር የመገንባት ስራ እየተከናወነ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

በየሻምበል ምህረት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.