አካል ጉዳተኞች በሚፈለገው መልኩ ከአድሎና መገለል ነፃ መሆን እንዳልቻሉ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 24፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) አካል ጉዳተኞች አሁንም በሚፈለገው መልኩ ከአድሎና መገለል ነፃ መሆን እንዳልቻሉ ተገለፀ፡፡
ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ32ኛ ጊዜ “የአካል ጉዳተኞችን የመሪነት ሚና በማጉላት አካታችና ዘላቂ ልማትን እናረጋግጥ” በሚል መሪ ሃሳብ በሀዋሳ ከተማ እየተከበረ ነው።
በበዓሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር )፣የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን፣ የሁሉም ክልሎች የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊዎች፣ የአካል ጉዳተኞች ማህበራት ተወካዮችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡
በመድረኩ÷ እንደሀገር አካል ጉዳተኞችን ለማሳተፍ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች ቢኖሩም አሁንም በሚፈለገው መልኩ አካል ጉዳተኞች ከአድሎና መገለል ነፃ መሆን አልቻሉም ነው የተባለው።
በትምህርት፣ በሥራ፣ በመረጃ፣ በጤና አገልግሎቶች፣ በልማት ፕሮግራሞች፣ በትራንስፖርት አና ሌሎች መሰል ጉዳዮች አሁንም መድሎና መገለል እየደረሰባቸው መሆኑም ተገልጿል።
እነዚህን ችግሮች ለመፍታት አካታችና አሳታፊ የሆኑ አበረታች ሥራዎች እየተከናወኑ ቢሆንም ሥራው በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት መገለፁን ኢዜአ ዘግቧል፡፡