Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትንና ጽንፈኝነትን ለመዋጋት ቁርጠኛ መሆኗን ገለጸች

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 24፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ቀጣናዊ ትብብርን በማጠናከር ሽብርተኝነትንና ጽንፈኝነትን ለመዋጋት ቁርጠኛ መሆኗን አስታወቀች።

በአፍሪካ ሕብረት እና የተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ሂሩት ዘመነ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ በአልጄሪያ ኦራን በተካሄደው 11ኛው አመታዊ የሰላም እና ደህንነት ጉባኤ ተሳትፏል።

አመታዊ ጉባኤው በአልጄሪያ እና የአፍሪካ ህብረት የሰላ እና ደህንነት ካውንስል የተዘጋጀ ሲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰላም እና ደህንነትን ለማረጋገጥ ተግዳሮት በሚሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ መምከሩም ተነግሯል፡፡

የአልጄሪያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አህመድ አታፍ ሰላም እና ደህንነትን ለማረጋገጥ ጉባኤው በአንድነት መዘጋጀቱ በጎ ሚና አለው ብለዋል፡፡

የጅቡቲ የውጪ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር እና የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት የሰላም እና ደህንነት ካውንስል ሰብሳቢ ማሃሙድ አሊ ዮሱፍ በአፍሪካ አህጉር የሚታዩ የሰላም እና ደህንነት ተግዳሮቶችን አንስተዋል፡፡

ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች እና የገንዘብ ችግር ሰላምን ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት ተግዳሮት መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

አምባሳደር ሂሩት ዘመነ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ቀጣናዊ ትብብርን ለማጠናከር እና ሽብርተኝነትን እንዲሁም ጽንፈኝነትን ለመዋጋት ቁርጠኛ መሆኗን መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመልክቷል።

ለማሳያ ያህል አሸባሪው አል-ሻባብ በቀጣናው ውድመት እንዳያደርስ ኢትዮጵያ በርካታ መስዋዕትነት መክፈሏን በመጥቀስ ሀገሪቱ በቀጠናው ሸብርተኝነትን በመዋጋት ረገድ ግንባር ቀደም ነች ብለዋል፡፡

በዘንድሮው ጉባኤ ሽብርተኝነትና ጽንፈኝነትን ማስወገድ እና ለአፍሪካ የሰላም እና ደህንነት ጉዳዮች ዘላቂ የገንዘብ ምንጭ ማግኘት ውይይት የተደረገባቸው ጉዳዮች መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.