Fana: At a Speed of Life!

አርሰናል ከማንቼስተር ዩናይትድ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 25፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የ14ኛ ሣምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ-ግብሮች ሲደረጉ ምሽት 5 ሠዓት ከ15 ላይ አርሰናል በኤምሬትስ ከማንቼስተር ዩናይትድ ጋር የሚያደርጉት ፍልሚያ በጉጉት ይጠበቃል፡፡

በቡድኖቹ መካካል በተለይም ከፈረንጆቹ 1996 እስከ 2004 የነበረው ብርቱ ፉክክር÷ በእንግሊዝ እግር ኳስ ታሪክ ቀደም ሲልም ሆነ ከዚያ በኋላ ያልተደገመ ነው በሚል በርካቶች ያነሳሉ፡፡

ይሁን እንጅ ቡድኖቹ በሂደት ከፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ፉክክር መራቀቸው ቀደም ሲል በመካከላቸው የነበረውን የፉክክር ግለት ቀንሶት እንደቆየም ይነገራል፡፡

የለውጥ መንገዳቸውን በስፔናዊው አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ የጀመሩት መድፈኞቹ÷ ባለፉት ሦስት ዓመታት ለፕሪሚየር ሊጉ ዋንጫ ክብር ከጫፍ ደርሰው ሳይሳካቸው ቀርቷል፡፡

እንዲሁም ማንቼስተር ዩናይትድን ከስኮትላንዳውዩ ስመጥሩ ስኬተማ አሰልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉስን በኋላ ወደ ቀድሞ ክብሩ የሚመልሰው አልተገኘም፤ በዚህ ሂደትም አሰልጣኝ በመቅጠርና በማሰናበት ውጥረት ለበርካታ ዓመታት ኳትኗል፡፡

ከሆላንዳዊው አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ ስንብት በኋላ በተሾሙት ፖርቹጋላዊ አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም እየተመሩ በመነቃቃት ላይ የሚገኙት ቀያይ ሰይጣኖቹ ዛሬ ለአርሰናል ፈተና ሊሆኑ እንደሚችሉም ተገምቷል፡፡

በ13ኛ ሣምንት የፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታዎች ሁለቱም ቡድኖች ተጋጣሚዎቻቸውን በሰፊ የግብ ልዩነት ማሸነፋቸው ደግሞ የዛሬውን ጨዋታ በይበልጥ ተጠባቂ አድርጎታል፡፡

አርሰናል ከፕሪሚየር ሊጉ መሪ ሊቨርፑል ላለመራቅ እንዲሁም ማንቼስተር ዩናይትድ በአዲሱ አሰልጣኝ ያገኘውን የአሸናፊነት ስሜት ይዞ ለመቆየት ጨዋታውን የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ ገብተው እንደሚጫወቱ ተነግሯል፡፡

ሌሎች የሊጉ የዛሬ መርሐ-ግብሮች ሲቀጥሉ÷ ምሽት 4 ሠዓት ከ30 ላይ ኤቨርተን ከዎልቭስ፣ ማንቼስተር ሲቲ ከኖቲንግሃም ፎረስት፣ ኒውካስል ዩናይትድ ከሊቨርፑል እንዲሁም ሳውዝሃምፕተን ከቼልሲ የሚፋለሙ ይሆናል፡፡

እንዲሁም ምሽት 5 ሠዓት ከ15 ላይ አስቶንቪላ ከብሬንትፎርድ እንደሚጫወቱ የወጣው መርሐ-ግብር ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.